በጾም ወቅቶች የሚደረጉ ሰናይ ምግባራት በአዘቦት ጊዜያትም ሊጠናከሩ ይገባል - የሃይማኖት አባትና ምዕመናን - ኢዜአ አማርኛ
በጾም ወቅቶች የሚደረጉ ሰናይ ምግባራት በአዘቦት ጊዜያትም ሊጠናከሩ ይገባል - የሃይማኖት አባትና ምዕመናን

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 15/2015 (ኢዜአ):- በጾም ወቅቶች የሚደረጉ ሰናይ ምግባራት በአዘቦት ጊዜያትም ሊጠናከሩ እንደሚገባ የሃይማኖት አባትና ምዕመናን ተናገሩ።
የሰዎች እርስ በእርስ መረዳዳት፣ መተሳሰብና መተዛዘን ዘመናትን የተሻገሩ ማኅበራዊ እሴቶች በተለይም በሃይማኖታዊ በዓላትና አጽዋዕማት ወቅት ይዘወተራሉ።
እነዚህ በጎ ተግባራት መንፈሳዊ ይዘት ኑሯቸው በተለያዩ የጾም ወቅቶች ይዘውተሩ እንጂ በአዘቦት ወቅት ሊቋረጡ የማይገባቸው መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ-ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ መላከ ሠላም ቆሞስ አባ ቃለ-ጽድቅ መረዳዳትና መተጋገዝ ሁሉም ሊተገበር የሚገባው በጎ ተግባር ነው ብለዋል።
ቤተክርስቲያኗ የፍልሰታን ጾም ጨምሮ በሁሉም አጽዋማት ወቅት ከጸሎቱ ጎን ለጎን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት እንዲዳብር አበክራ እያስተማረች መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የወገኖቻቸውን ድጋፍና እገዛ የሚሹ ዜጎች በብዛት ያሉበት ወቅት መሆኑን መረዳትና መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህም የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በአጽዋማት ወቅት ብቻ መሆን የለበትም ያሉት አባ ቃለ ጽድቅ ተግባሩ በየትኛውም ወቅት ላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በበኩላቸው የፍልሰታ ጾም ልዩ የሱባኤ፣ የጾምና ጸሎት ወቅት ነው ብለዋል።
ከጾም ጸሎቱ ጎን ለጎን ደግሞ ያላቸው ለሌላቸው ድጋፍ የሚያደርጉበትና የሚተጋገዙበት መሆኑም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የወገኖቻቸውን ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ያሉበት በመሆኑ ከጾም ወቅት ባሻገርም እየተከናወነ ያለውን የመረዳዳት እሴት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ማስተዋል ዓለሙ፤ በፍልሰታ ጾም ወቅት ሕብረተሰቡ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል እንዳለው አንስታ ይህንን በጎ ተግባር ማስቀጠል ይገባል ብላለች።
እርሷም አቅሟ በፈቀደው መጠን የተቸገሩትን በመደገፍና በመርዳት ለወገኗ የምታደርገውን መልካም ተግባር ለማስቀጠል የበኩሏን እንደምታደርግ በመጠቆም።
የተቸገሩ ወገኖችን መደግፍና ማገዝ በጾም ወቅት አንዱ ሃይማኖታዊ ምግባር ነው፤ ይህንን ከጾም ወቅት ውጪ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሰናይት አበበ ናቸው።
ወይዘሮ አየለች ገብሬም በጾም ወቅት የሚስተዋለው የመደጋገፍና የመተጋገዝ ባህል ሊዳብረ የሚገባው መሆኑን ገልጸው ለዚህም የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።