ቀጥታ፡

"ባልጠበቅኩትና ባላሰብኩት ጊዜ ቤቴን ለማደስ ለመጡ በጎ ሰዎች ትልቅ ምስጋና አለኝ'' -- የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቤት ተጠቃሚዎች

ቦንጋ፣ ነሀሴ 15 /2015 (ኢዜአ):- "ባልጠበቅኩትና ባላሰብኩት ጊዜ ቤቴን ለማደስ ለመጡ በጎ ሰዎች ትልቅ ምስጋና አለኝ'' ሲሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቤት ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጀነር ነጋሽ ዋጌሾ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በክልሉ ቦንጋ ከተማ የ14 አቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታ አስጀምረዋል።

በክረምትና በጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተተገበሩ ከሚገኙት በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት እድሳትና ግንባታ በርካቶችን ከችግር እያላቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መኖሪያ ቤታቸው ከሚታደስላቸው አረጋዊያን መካከል አንዷ ወይዘሮ ፋጡማ አባቡልጉ ሲሆኑ "ባልጠበቅኩትና ባላሰብኩት ጊዜ ቤቴን ለማደስ ለመጡ በጎ ሰዎች ትልቅ ምስጋና አለኝ'' ብለዋል።

ቤታቸው ከማርጀቱ የተነሳ በክረምት ወቅት ዝናብ ሲዘንብ ቅዝቃዜው እንዲሁም ወደ ቤት የሚገባው ፍሳሻ ለበሽታ ይዳርጋቸው እንደነበረ የገለፁት ወይዘሮ ፋጡማ ቤታቸው ሲታደስ ከችግራቸው እንደሚላቀቁ ተስፋ አድርገዋል። 

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ተሳታፊ የሆነው የወጣት መሳፍንት ሲሳይ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህሊና እርካታ የሚሰጠው፣ ከየትኛውም ስራ አብልጦ የሚያየው ተግባር መሆኑን ገልጿል።

በተለይም እንዲህ ዓይነት አቅመ ደካማና ጧሪ ላጡ ዜጎች የሚደረግ ድጋፍ የሚሰጠው እርካታ ባለፈ ዜጎች እርስ በርስ ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር ያስችላል ነው ያለው። 


 

የወይዘሮ ፋጡማ አባቡልጉን ቤት ጨምሮ ቦንጋ ከተማ የ14 አቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታ በዛሬው ዕለት ያስጀመሩት የደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጀነር ነጋሽ ዋጌሾ አገልግሎቱ የበርካታ ዜጎች ችግር እየፈታ ነው ብለዋል።

ይህ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በአገልግሎቱ የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመጠገን ባለፈ ትምህር ቤቶችን እና የጤና ተቋማትን የመገንባት ትልልቅ ተግባራትን እየተከናወኑ እንደሆነ አንስተው ህብረተሰቡም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ዛሬ የተጀመሩ ቤቶች በቀጣይ 30 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።

በክልል ተቋማት የተጀመረው የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ በዞንና በወረዳ እንዲሁም በከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ህብረተሰብን በማስተባበር መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በክልሉ ከ601 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እየተሳተፉበት የሚገኘው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የቤት ግንባታና ዕድሳት ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም