ቀጥታ፡

ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል ለወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትና ዕድገት በትኩረት ይሰራል - አምባሳደር ግርማ ብሩ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ):- የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ለወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትና ዕድገት መንግስት በትኩረት የሚሰራ መሆኑን በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለጹ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 3 ነጥብ 64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ የ2015 በጀት ዓመት አፈፃጸምን አስመልክቶ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የወጪ ምርት ላኪ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የ2015  በጀት ዓመት የወጪ ምርት ንግድ ከ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በወጪ ምርት ላይ የተመዘገበው የአፈፃጸም ልዩነትም በማዕድን፣ በጫት እና በቡና ዘርፎች ላይ የተስተዋለው የምርት ማነስ፣ የውጭ ገበያ መቀዛቀዝና ኮንትሮባንድ መሆኑን ተናግረዋል።

የወጪ ምርት የአቅርቦት ሰንሰለት ያለው መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ግርማ ብሩ፤  ለዘርፉ መሻሻል ችግሮችን በመለየት ቀጣይነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫ መከተል እንደሚስፈልግ አንስተዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ለችግሩን ምላሽ ለመስጠትም መንግስት ቀጣይነት ያለው ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። 

በጥራጥሬ ምርቶች ላይ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ አፈፃጸም መመዝገቡን አድንቀው፤ በጫት፣ በቁም እንስሳትና በቡና ወጪ ምርቶች ያለውን ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባ አንስተዋል።

መንግስትም የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ህገ-ወጥ እና የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለማስቆም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፤ በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 5 ነጥብ 21 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር ገቢ  ተገኝቷል ብለዋል።

አፈጻጸሙ የዕቅዱን 69 ነጥብ 79 በመቶ እንደሆነም ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ውጫዊ እና ተቋማዊ የውስጥ ችግሮች የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንቅፋት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

ከላኪዎች ጋር የተደረገው የአፈፃጸም ግምገማ የምክክር መድረክም በስራ ሂደት  የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በ2016  በጀት ዓመት የወጪ ምርቶችን ጥራት እና መጠን በማሳደግ ከ5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩም ከኮንትሮባንድ፣ ከንግድ አሰራር፣ ህገ-ወጥነት፣ ከድጋፍና ክትትል፣ ከገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲ እና ተያያዥ የወጪ ንግድ አፈፃጸም ጉድለት ላይ በቀረቡ ሃሳቦች በውይይቱ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም