ቀጥታ፡

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ በቀጣይ ሁለት ወራት ዳግም በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል

 አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ)፡- የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ በቀጣይ ሁለት ወራት በሙሉ አቅሙ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተገለጸ።

በ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነባውና ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል በመቀየር ለከተማዋ ችግር መፍትሔ ይሰጣል የተባለው ረጲ ደረቅ ቆሻሻ  2011 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።

የከተማውን 50 በመቶ ቆሻሻ ወደ ሀይል የሚለውጠው ፕሮጀክት 25 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን  በመለዋወጫ  እጥረት ሳቢያ በተለያየ ጊዜ ምርት የማምረት ስራው ሲቆራረጥ እንደነበር ይታወሳል።

በተጨማሪም ለአንድ አመት ከሶስት ወር ያህል ኃይል የማመንጨት ስራውን አቋርጦ የነበረ ሲሆን ከግንቦት ወር 2015 ጀምሮ  በግማሽ አቅሙ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

የኃይል ማመንጫው ስራ አስኪያጅ ብሩክ ኤባ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኃይል ማመንጫው በተርባይን ላይ በደረሰ መጠነኛ ችግር ምክንያት ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ አመት ከሶስት ወር የኤሌክትሪክ ኃይል ሳያመርት ቆይቷል ።

በእነዚህ ጊዜያት ቆሻሻ በማቃጠል ለአዲስ አበባ ፅዳት አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው ከግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ  ተርባይኑ ተጠግኖ ወደ ስራ መግባቱን  ገልፀዋል።

በዚህም ኃይል ማመንጫው 12 ነጥብ 5 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ተናግረዋል።

 ኃይል ማመንጫው አሁን ላይ በአንድ ቦይለር (ቆሻሻ ማቃጠያ) በግማሽ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ሁለተኛውን ቦይለር ጠግኖ ወደስራ ለማስገባት መለዋወጫ ታዞ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል። 

 በሁለት ወር ውስጥ በመረከብ ቦይለሩ ተጠግኖ ኃይል ማመንጫው በሙሉ አቅሙ ኃይል ያመርታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። 

ይህም ኃይል ማመንጫው በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት በማድረግ 25 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ያስችለዋል ብለዋል።

በቀጣይም ኃይል ማመንጫው ስራውን በዘላቂነት እንዲያከናውን ከመለዋወጫ ጋር የሚገጥመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል። 

ኃይል ማመንጫው ስራ ከጀመረበት አንስቶ ጊዜ ለአንድ አመት ያህል በውጭ ባለሙያዎች ስራውን ሲያከናውን ቆይቶ ከ2012 ዓ.ም አንስቶ ስራውን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እያከናወነ ነው። 

ኃይል ማመንጫው ኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በመዲናዋ በአማካይ በቀን ከሚሰበሰበው 2 ሺህ 500ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 1 ሺህ 280 ቶን ያህሉን የማቃጠል አቅም ያለው ሲሆን አሁን በአንድ ቦይለር 640 ቶን ቆሻሻ በማቃጠል ለከተማዋ ፅዳት አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም