ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት  የህዝብን ችግር ለመፍታት እያገዙ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ቦንጋ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  እየተካሄዱ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የህዝቡን ችግር ለመፍታት እያገዙ መሆናቸውን የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  በቦንጋ ከተማ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚገነቡ የ14 አቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወደ ስራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ  ህብረተሰቡንና ሀገርን የሚጠቅሙ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የበርካታ ነዋሪዎችን ችግር ለመፍታት በማገዝ እፎይታ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።


 

የአረጋዊያን ቤት ግንባታና እድሳት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ አካል እንደሆነ ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስትም በዚህ ተግባር ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አምና በቦንጋ ከተማ አምስት ቤቶችን መጠገን መቻሉን አንስተው፤ ዘንድሮ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ 14 ቤቶችን ለመገንባት  ስራ መጀመሩን አረጋግጠዋል።

ይህ ተግባር በቦንጋ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም  የክልሉ አካባቢዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።


መንግስት በመነሻነት ይህን ተግባር እያከናወነ ቢሆንም ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ባለሀብቱ፣ ወጣቱና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል እያደረጉት  ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።


የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ፣ ዛሬ አረጋዊያን የሆኑ እናት አባቶቻችን ትናንት በወጣትነትና በጉብዝና ዘመናቸው ጠንካራ ከመሆንም ባለፈ ሌሎች አቅመ ደካሞችን ሲረዱ የነበሩ ናቸው ብለዋል።


እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አቅም እየቀነሰ መሄዱ የተፈጥሮ ህግ ነው ያሉት ከንቲባው፤  እነዚህ የሀገር ባለውለታዎችን ከችግር ለማውጣትና ከጎናቸው ለመቆም በማሰብ  የቤት ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰዋል።


በየክረምት የሚከናወኑ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር የሆኑ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል። 


በከተማው የፌደራል ተቋማትና የክልሉ መንግስት ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ  በበጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም አቶ አስማማው አንስተዋል።


በዚህም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በክረምቱ 14 የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ለማደስ ቃል በገቡት መሰረት ዛሬ ስራውን በመጀመራቸው ከንቲባው  ምስጋና አቅርበዋል።


የከተማው አስተዳደርም ቤቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠው፤ ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።


የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት መካከል የአቅመ ደካሞች ቤቶችን መጠገን አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


ይህ ተግባር ጎጇቸውን በራሳቸው መቀለስና ማደስ ለማይችሉ ወገኖችን ከችግር ለማውጣት ሁነኛ መንገድ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ሊሳተፍበት ይገባል ብለዋል።


በክልሉ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ601 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ የችግኝ ተከላ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ዕድሳትን ጨምሮ ሌሎችም የተለያዩ ተግባራት  እየተከናወኑ እንደሚገኙ  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም