ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ከታክስ በፊት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በ2015 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ  በደፋይናነስ ስራዎች አፈጻጸም 47 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 42 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ገልጿል።

ተቋሙ ይህን ያለው የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ እንዳሉት፤ ኮቪድ 19፣ የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፣ የሀገር ውስጥ የፀጥታ ችግርና ሌሎችም ጫናዎች በድርጅቱ ስራዎች ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፉም የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

በበጀት ዓመቱ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ከተጓጓዘው 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን እቃ ውስጥ 34 በመቶውን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ  ማጓጓዙን ገልፀዋል። 

በመርከብ የወጪ ጭነትና ጥቅል ጭነት አገልግሎት በዕቅዱ ልክ መፈፀሙን ጠቅሰው፣ በብረት ማጓጓዝ ረገድ ግን ዝቅተኛ አፈፃፀም እንደነበር አውስተዋል። 

185  የጭነት አስተላላፊ መኪናዎችን ገዝቶ ወደ ስራ በማስገባት ከጅቡቲ-አዲስ አበባ ዕቃ የማጓጓዝ ስራዎችን ከዕቅድ በላይ መፈፀም እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

በዩኒ ሞዳል እና በመልቲ ሞዳል፣ በወደብና ተርሚናል አገልግሎት፣ በወጪ ዕቃ ማጓጓዝ፣ በመጋዘን አገልግሎት በአብዛኛው ከዕቅዱ በላይ መሳካቱን ገልፀዋል።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከአገልግሎቶቹ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉንም ነው የተናገሩት።

በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድ 500 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ 480 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን አንስተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ወደብ ላይ በደረሰ ጊዜ በፍጥነት ወደሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ ሰፊ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ መርከብ ወኪሎች ቀልጣፋ አገልግሎት አለመስጠት፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ቅንጅታዊ ችግር፣ የደንበኛ ዕቃ ስርቆትና ቅሸባ፣ የግዥ መጓተት፣ የጨረታና ግዥ ስርዓት ኋላቀርነት፣ ዲጂታላይዜሽንና አውቶሜሽን ችግሮች መስተዋላቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ ይህን መቅረፍ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የተቋሙን የተፈቀደ ካፒታል ማሳደግ፣ ከወደብ ወደ ወደብ ንግድ ማስፋፋት፣ የጭነት አቅምን ማሳደግ፣ ያልተከፈሉ ክፍያዎችን ማስመለስ፣ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ፣  ወደብና ተርሚናልን በቴክኖሎሎጂ ማዘመን የ2016 ትኩረቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የላሙ ወደብን ጨምሮ አማራጭ ወደቦችን ማስፋፋት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ደረቅ ወደብ ማስፋፋት፣ ተጨማሪ መርከብ ግዥ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም