ቀጥታ፡

"አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና" ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍ ሚና የሚያጎለብት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ) ፡- በአዲስ አበባ በጎተራ አካባቢ የሚገነባው "አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና" የልማት ፕሮጀክት የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ሚና የሚያጎለብት ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ በ600 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው "አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና" ለመገንባት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

ግንባታውን ለማስጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቻይናው የግንባታ ኩባንያ 'ቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ' ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።

በመዲናዋ በጎተራ አካባቢ የሚገነባው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በውስጡ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የትምህርት፣ የባህል፣ የፋይናንስና የቢዝነስ ዞን ያካትታል ተብሏል።

 


 

በተጨማሪም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤትና መዝናኛ ዞኖች እንደሚኖሩት ተመላክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ፕሮጀክት የሚሆን 35 ሄክታር መሬት በወቅታዊ የሊዝ ዋጋ አስልቶ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

የቻይናው የግንባታ ኩባንያ 'ቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ' ወቅቱ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስና ሌሎች ግብዓት በማቅረብ ግንባታውን ያካሄዳል ተብሏል።

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አዲስ አባባ ከተማን ለኑሮና ለሥራ ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ይህንን እቅድ እውን ለማድረግ አስተዳደሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን አቅዶ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።


 

እነዚህ ፕሮጀክቶች ዘመን ተሻጋሪ፣ ለዜጎች ሥራ እድል የሚፈጥሩና ከተማዋ ዓለም አቀፍ ሚናዋን ላቅ የሚያደርጉ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በመዲናዋ ለመገንባት ዛሬ ሥምምነት ላይ የተደረሰው አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናም የዚሁ አካል መሆኑን ከንቲባዋ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በበኩላቸው የቻይናና የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም ሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር አንዱ መሳያ ነው ብለዋል።

በከተማዋ የሚገነባው "አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና" የልማት ፕሮጀክትም የሁለቱ አገራትን ትብብር ለማጠናከር ተጨማሪ እድል ይሰጣል ነው ያሉት።

አዲስ አበባን ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ቻይና ትብብሯን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም