የአዲሱ ክልል አስተዳደራዊ መዋቅር ወደ ህዝቡ ይበልጥ በመቅረቡ ፍትሃዊ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ ዕድገትን የሚያፋጥን ነው --የመሥራች ጉባዔው ተሳታፊዎች

233

አርባ ምንጭ ፤ ነሐሴ 14/2015 (ኢዜአ) የአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተዳደር መዋቅሩ ወደ ህዝቡ ይበልጥ በመቅረቡ ፍትሃዊ የአገልግሎት ተደራሽነት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፤ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕድገት የሚያፋጥን ነው ሲሉ የክልሉ መሥራች ጉባዔ ተሳታፊዎች ገለጹ።
 
ክልሉ ያለውን ሰፊ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ፈጥኖ እንዲለማና በገቢ ራሱን እንዲችል ጥረት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
 
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገሪቱ 12ኛው ክልል ሆኖ ትናንት በይፋ ተመሥርቷል። በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ ለነበሩ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

 
ይህን ተከትሎ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ተወካዮች እንደተናገሩት የክልሉ መመስረት የሕዝብ አስተዳደርና ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
 
የክልሉ መንግሥት ያዋቀራቸው ዞኖችና ወረዳዎች ደግሞ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአካባቢ ደረጃ ለመፍታት ያግዛሉ ብለዋል።

ከደራሼ አካባቢ የተወከሉት አቶ ነፃነት ኃይሉ፣ መንግሥት የህዝቡን አዳጊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለአካባቢዎች አቅም የሚመጥን አደረጃጀት በመፍቀዱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አካባቢው በልማትና በአገልግሎት ተደራሽነት ችግር በሚገባው ልክ ሳያድግ መቆየቱን ተናግረዋል ።

አካባቢው ራሱን በገቢ ለመቻል የታክስ መሠረቶችን በማስፋት፣ የቱሪዝም ሀብቶችን በማሳደግ ብሎም ምርትና ምርታማነት በመጨመር የኢኮኖሚ አቅሙን ለማጎልበት እንደሚሰራ አቶ ነጻነት ጠቁመዋል።

ከባስኬቶ አካባቢ የተወከሉት አቶ ዱጼ ታምሩ በበኩላቸው የክልሉ መመስረት የህዝቡ የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሲቀርብ የነበረው የአደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ እንደሰጠ ገልጸዋል።

በዚህም የአስተዳደር መዋቅሩ ወደ ህዝቡ ይበልጥ የቀረበና ፍትሃዊ የአገልግሎት ተደራሽነት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፤ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕድገት ያፋጥነዋል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመስረቱ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከአማሮ አካባቢ የተወከሉት አቶ ጢሞቲዎስ በቀለ ናቸው።

የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል ከክልሉ የተለያዩ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም አቶ ጢሞቲዎስ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገሪቱ 12ኛው ክልል ሆኖ ትናንት በይፋ የተመሠረተ ሲሆን፣ በክልሉ በሥሩ ለሚገኙ ሰባት አስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

ልዩ ወረዳ የነበሩት የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ፣ የቡርጂ፣ የአሌ ልዩ ወረዳዎች እያንዳንዳቸው ራሳቸውን ችለው በዞን እንዲደራጁ ወስኗል። 

በተጨማሪም የኮንሶ ዞን ኮልሜ ቀበሌ በወረዳ ደረጃ እንዲደራጅ እንዲሁም የደቡብ ኦሞ ዞን በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ  ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም የማሌ፣ የሐመር፣ የበና ጸማይ፣ የሰላማጎ፣ የኛንጋቶም፣ የዳሰነች ወረዳ እና የቱርሚ ከተማ አስተዳደር በጋራ በአንድ ዞን ይደራጃሉ። 

ቀሪዎቹ የደቡብ አሪ፣ የወባ አሪ፣ የባካ ዳውላ፣ የሰሜን አሪ ወረዳዎች እንዲሁም የጂንካ ከተማ አስተዳደር እና የገሊላ ከተማ አስተዳደር  በሌላ ዞን  እንዲደራጁ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም