ለዘመናት የቆዩና ለጠንካራ ትስስር ምሰሶ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ሳይሸረሸሩ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘመናት የቆዩና ለጠንካራ ትስስር ምሰሶ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ሳይሸረሸሩ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 14/2015 (ኢዜአ)፡- ለዘመናት የቆዩና ለጠንካራ ትስስር ምሰሶ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ሳይሸረሸሩ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "ሀገራዊ እሴቶቻችን ለጠንካራ ሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት ለዘመናት ለቆየው ጠንካራ የህዝቦች ትስስር ምሰሶ የሆኑት ዕሴቶቻችን ሳይበረዙና ሳይሸረሸሩ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ ታደሰ እንዳሉት ባህላዊ እሴቶች እንደ ሀገር ለዘመናት ያቆዩን ናቸው።
እነዚህ ሀብቶች ሳይበረዙና ሳይሸረሸሩ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ሁሉም በተሰማራበት መስክ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ያለመግባባትና የሰላም እጦት ችግሮች መሰረታዊ መንስኤ እሴቶቹን በአግባቡ አለመጠቀም መሆኑን አንስተው፣ በእሴቶቹ ውስጥ ያለው ማህበራዊና አስተዳደራዊ አቅም በበቂ ሁኔታ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
መንግስት እሴቶች እንዳይጠፉ በመስኩ የሚሰሩ አካላትን ማበረታታት ምሁራንና ሌሎች ዜጎች ደግሞ በማስተማርና በዕሴቶች ዙሪያ በጥናት ላይ የተመሰረተ ውጤት በማቅረብ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።
እሴቶቹን በማዳበር ፖለቲካንና ታሪክን ከመቀላቀልና ከአላስፈላጊ ትርክቶች ወጥተን እሴቶቻችንን አጎልብተን ትስስራችንን ማጠናከር ይገባናል ሲሉም ምሁሩ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።
በየማህበረሰቡ የሚገኙ ዕሴቶች መብትን የመጠየቂያ ብቻ ሳይሆኑ የማህበራዊ ሃላፊነት ጭምር ያለባቸው መሆኑን ያወሱት ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ፣ “እኔም እነዚህ እሴቶች እንዳይሸረሸሩ ጥናትና ምርምር በማድረግ አግዛለሁ” ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የሶሲዮሎጂ ተማሪዋ ወጣት ነሲባ ሀሰን በበኩሏ የወጣችበት የሶማሌ ማህበረሰብ ግጭቶች ሲያጋጥሙ የሚፈታበት “ሄር” የተሰኘ ባህላዊ እሴት እንዳለ ገልጻለች።
በዚህ እሴት ማንኛውም ግጭትና ለግጭት መንስኤ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ ችግር ሲያጋጥም የሀገር ሽማግሌዎች ሁሉንም አካላት በማነጋገር ግራ ቀኙን አይተው አደጋ ከመከሰቱ በፊት የሚፈቱበት እሴት መሆኑን ተናግራለች።
“እኔ ከሌላ አካል ጋር ግጭት ውስጥ ብገባ እንኳን መጀመሪያ ነገሮቹን ከምንጩ በመለየት አገናዝቤ ባህላዊ እሴቴ በሚያዘው መሰረት የተሻለውን መፍትሄ እወስዳለሁ” ብላለች።
በሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አባል አቶ ተገኝ ወልዴ እንዳሉት ሀገራዊ ባህላዊ እሴቶች ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷና የህዝቦች ሰላም ተጠብቆ በጋራ ለመኖር አስችሏታል።
“እነዚህ እሴቶቻችን ለሰላምና በሰላም ለመኖር ያላቸው ፋይዳ እጅግ ትልቅ ነው። በዚህም ኖረንበታል። ሀገራችንን በሰላም አስጠብቀን እስከዛሬ የኖርነው ለእሴታችን በመገዛታችን ነበር” ብለዋል።
ነባር እሴቶችን ለመመለስና ከምዕራባውያን ባህል ተጽዕኖ ለማላቀቅ ሁሉም ድርሻውን መወጣት እንዳለበት ይገባል ያሉት አቶ ተገኝ፣ እሳቸውም የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተዘጋጀው የውይይት መድርክ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።