ቀጥታ፡

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፈው ባህር ዳር ከተማ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከአዛም ጋር ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2015 በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያው አዛም ክለብ ጋር ያካሂዳል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ ለጨዋታው በባህር ዳር እና አዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

በሴኔጋላዊው የ43 ዓመት አሰልጣኝ የሱፍ ዳቦ የሚመራው አዛም ክለብ በታንዛኒያ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገብቷል።

ሶማሊያዊው ሀሰን መሐመድ ሀጂ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።

ክለቦቹ የመልስ ጨዋታቸውን ነሐሴ 21/2015 በታንዛኒያ ያደርጋሉ።

በደርሶ መልስ ያሸነፈው ክለብ በቀጣዩ ዙር ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር ይጫወታል።

ባህር ዳር ከተማ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፈው በ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም