በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን ውሎ የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን ውሎ የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2015 (ኢዜአ) ፡- በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው 19ኛው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን ውሎ የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይከናወናል።
የፍጻሜው ውድድር የሚከናወነው ከምሽቱ 1 ሰአት ከ25 ደቂቃ ላይ ነው።
አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና አትሌት ይስማው ድሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ሰለሞን 26 ደቂቃ 46 ሴኮንድ ከ13 ማይክሮ ሴኮንድ፣ አትሌት በሪሁ አረጋዊ 26 ደቂቃ ከ44 ደቂቃ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ እና አትሌት ይስማው 27 ደቂቃ ከ8 ሴኮንድ 85 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።
የዩጋንዳው ጆሹዋ ቼፕቴጋይ እንዲሁም ኬንያውኑ አትሌቶች ኒኮላስ ኪፕኮሪር እና በርናርድ ኪቤት የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ ከምሽቱ 12 ሰአት ከ5 ደቂቃ ላይ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና አትሌት ሂሩት መሻሻ ለፍጻሜ ለማለፍ ይወዳደራሉ።
ትናንት ማምሻውን በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተካሄደው የፍጻሜው ውድድር አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና አትሌት እጅጋየሁ በመውጣት ኢትዮጵያ ሶስቱንም ሜዳሊያዎች ጠራርጋ እንድትወስድ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በ1 የወርቅ፣1 የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
አሜሪካ በ2 የወርቅና በ1 የነሐስ ሜዳሊያ አንደኛ ደረጃን ይዛለች።
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ነሐሴ 21/2015 ይቆያል።