በአውደ-ርዕዩ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ ማገዶ ቆጣቢ አዳዲስ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ይተዋወቃሉ - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ - ኢዜአ አማርኛ
በአውደ-ርዕዩ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ ማገዶ ቆጣቢ አዳዲስ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ይተዋወቃሉ - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 13/2015 (ኢዜአ) ፦ በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው አውደ-ርዕይ የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ የሚያሻሽሉ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ ማገዶ ቆጣቢ አዳዲስ የኃይል አማራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚተዋወቁ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች "የውሃ ኃብታችን ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን የውሃና ኢነርጂ አውደ-ርዕይ ጎብኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ኃብት መካከል የውሃ ኃብቷ ግንባር ቀደም ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
በዚህም የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን በማልማት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ለማሳየት በሳይንስ ሙዚየም አውደ-ርዕይ ተዘጋጅቶ ለዕይታ ክፍት መሆኑን ገልፀዋል።
በአውደ-ርዕዩ ላይም በትልልቅ ግድቦች ከሚገኘው የኃይል አማራጭ ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማስፋት በከተማና በገጠሩ የሚኖሩ እናቶችን ጫና ለማቃለል የተሰሩ ሥራዎች መቅረባቸውን ጠቁመዋል።
በአውደ-ርዕዩ ላይ የለሙና በመልማት ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ የገፀ እና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲሁም የኢነርጂ አቅሞችን በመለየት ዜጎች እንዲመለከቷቸው መቅረባቸውን አንስተዋል።
በውሃና ኢነርጂ አውደ-ርዕዩም የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ በማሻሻል አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ ማገዶ ቆጣቢ አዳዲስ የኃይል አማራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚተዋወቁበት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በውሃና ኢነርጂ አውደ-ርዕዩ ላይ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ በውሃ ኃብት አስተዳደር እና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ተሰናስለው ለዕይታ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መጎብኘት ያልቻሉ ዜጎችም ከሥፍራው ተገኝተው የሚጎበኙትን ያህል ስሜት በሚሰጥ መልኩ "በቨርቹዋል ሪያላይዜሽን" ቴክኖሎጂ ግድባቸውን መመልከት ይችላሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንም ለአንድ ወር የሚቆየውን የውሃና ኢነርጂ አውደ-ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ተገኝተው እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፤ ከኃይል ማስተላለፊያ የራቁ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሶላርና ባዮ ጋዝ የተሰሩ ልማቶች ለዕይታ ቀርበዋል ብለዋል።
በአነስተኛ ቴክኖሎጂ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ የልማት ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ በማድረስ ለመብራት፣ ለምግብ ማብሰያነትና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች መቅረባቸውንም አንስተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ አህመድ፤ የዜጎች የውሃና ኢነርጂ ፍላጎት እንዲሟላ ለተቋሙ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በአውደ-ርዕዩ የቀረቡት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፉ የመጠጥ ውሃ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የአየር ንብረት ትንበያ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን እንደተመለከቱም ገልፀዋል።
የውሃና ኢነርጂ አውደ-ርዕዩን ትናንት ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኸ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።
አውደ-ርዕዩ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የውሃና ኢነርጂ ኃብት እንዲሁም አቅም ለማሳየት ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለሚቀጥሉት 30 ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ይሆናል።