ቡሄ እና ትውፊቱ

 

በአየለ ያረጋል

 "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤

ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" 

ዛሬ ማታ ለጠበል ጠዲቅ እንዳትቀር ሲሉኝ ጎረቤቴ ደብረ ታቦርን አስታወሱኝ። እኔ ባደኩበት ገጠራማ አካባቢ ዛሬን (ነሐሴ 13) ደብረ ታቦር እንለዋለን። ይህ ዕለት በአብዛኛው ኢትዮጵያ አካባቢ 'ቡሄ' በሚል ይታወቃል።

የክረምት ወቅት ሦስተኛው ወርኅ ነሐሴ ነው። ቡሄ ደግሞ ከወርኅ ነሐሴ ውብ መልኮች አንዱ ነው። ትውፊታዊ አንድምታው ከክረምት ወደ ጥቢ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከጭጋግ ወደ ወገግታ...የመሸጋገር ምኞት ጋር ይቆራኛል። "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት" የሚባለውም ለዚህ ይመስላል። በገጠር በእርሻ ሲማስን የከረመ ለገበሬ እና በሬ ከቡሄ በኋላ እፎይታ ማግኘት ይጀምራል።

የክረምቱን ከባድ ወቅት አልፎ ጳጉሜን ተሻግሮ ተናፋቂው ወርኅ መስከረም ለመድረስ ('ነይ ብራ ነይ ብራ' እንዲሉ) የቡሄ ወቅት የጉጉት ሰሞን ነው። አዲስ ዓመትን ለማየት የመሻት ምልክት ነው። በነሐሴ አጋማሽና መገባደጃ የአርሶ አደሩ ማሳ ቡቃያ ይለብሳል። 

ቡሄ መሠረቱ ሃይማኖታዊ ቢሆንም እንደየአካባቢው መልከ-ብዙ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች አሉት። ቡሄ ታዳጊዎች ይናፍቁታል። በሃይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር (ታቦር ተራራ) ክብረ-መንግሥቱን እና ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ትዕምርት እንደሆነ ሊቃውንተ- ቤተክርስቲያን ይገልጻሉ።

የቡሄ ክዋኔዎች እና ስነ-ቃሎች

ሆያ…. ሆዬ….!ሆ….!

ቡሄ መጣ በዓመቱ፣ 

ኧረ እንደምን ሰነበቱ

እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል፣

አጋፋሪ ይደግሳል፤ ...

የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ ይበራል፡፡ ሕፃናቱ ጅራፍ ገምደው ያጮሃሉ። እናቶችም ስንዴ አጥበው እና ፈትገው ዳቦ ይጋግራሉ። ሙልሙል ያዘጋጃሉ። ቀዬው በሕፃናቱ ዜማ ድባብ ይሞላል። መንደሩ በ"ሆያ ሆዬ" ሕብረ- ዝማሬ ይደምቃል።

"ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ

ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ 

ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …" በሚለው።

ይህ ትውልድ ተሻጋሪ ትውፊት እሴቱና ልማዱ ቢለዋወጥም ዛሬም ይከወናል። ቡሄ ትርጉሙ 'ብራ' ማለት ነው። ከሙልሙል ዳቦ በማቆራኘትም 'መላጣ" ማለት ነው የሚሉም አሉ። የቡሄ ጭፈራ በሁሉም አካባቢዎች የተለመደ ነው። ሕፃናቱ ጨፍረው ሙልሙል ዳቦ ይቀበላሉ። ሙልሙል ሲሰጣቸው ምስጋና፣ ሙልሙል ካልተዘከሩ ደግሞ የሐሜት ስነ-ቃሎችን ያስከትላሉ።  

ለምሳሌ በቡሄ ጭፈራ ዳቦ ከቀረበላቸው

"... ሐሚና ሚና፤ ዘነዘነና የበር ዘነዘና 

ጌታዬን ያማ ሰው፤ እከክ ይውረሰው..." ሲሉ

ሙልሙል ያልጋገረች ሴት የተገኘች እንደሆነም  

"የቡሄ ዕለት ያልጋገረች ሴት፤ 

አንድ እግሯ ከቆጥ 

አንድ እግሯ ከረመጥ..." ይላሉ።

በነገረ ትውፊት ጽሑፎች የሚታወቁት ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ስለ 'ብሂለ ወራት' ከጠቀሷቸው ስነ-ቃሎች መካከል ወርኅ ነሐሴ እንዲህ ተጠቅሷል። 

...

" በሐምሌ እንዴት እከርማለሁ ደግሜ

በነሐሴ ነፍሴን እዣለሁ በጥርሴ

....

  ነሐሴን በእንጥርጣሪ፣ ሐምሌን በብጣሪ

ነሐሴ እግር በረቱ፣ መስከረም ዳገቱ

በግንቦት አተላ፣ በነሐሴ ባቄላ ..."

የቡሄ በዓል የብርሃን በዓል ማለት ነው። የብርሃኑ መገለጥ ዕለት ነው። በዚህም ነሐሴ 13 አመሻሽ ችቦ ይለኮሳል። የችቦው ትዕምርት ደግሞ አንዱ ለሌላው መካሪ አስተማሪ፣ አርዓያ፣ ምሳሌ፣ ብርሃን መሆኑን ያመላክታል። 

የጅራፍ ትውፊታዊ መልኩ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይሰጠዋል። ቀዳሚው ምስጢር የኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋትንና ሞቱን ሲሆን ሁለተኛው የጅራፍ ነጎድጓድ ድምፁ የባሕርይ አባቱን (የአብን) ምስክርነት ይወክላል።

    ነገረ-ሙልሙልም የራሱ ትውፊታዊ ትርጓሜ አለው። በችቦ ብርሃን ወላጆች እረኝነት የወጡ ልጆቻቸውን ለመፈለግ ሲወጡ ለልጆቻቸው በያዙት ስንቅ ይመሰላል። የሙልሙል ዳቦ ዝክሩ መተሳሰብን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ይወክላል። ዛሬም ዳቦ የሚጋገረው ለዚህ ትውፊት ነው። ታዳጊዎች 'ሆያ ሆዬ' እያሉ ሙልሙል ዳቦ የሚጠይቁትም ከዚህ ትውፊት የመነጨ ነው። በሌላ ጎኑ ሕፃናቱ በደቀመዛሙርት፣ ዝማሬያቸው ደግሞ  በ 'የምሥራች' እንዲሁም  ስጦታው በምርቃት ይመሰላል።

በዓለ-ደብረ ታቦር ወይም በቡሄ ትውፊታዊ ክዋኔዎች የየራሳቸው ትርጓሜ እና እሴት ቢኖራቸውም አልፎ አልፎ ከትውፊት ያፈነገጡ ክዋኔዎች ይስተዋላሉ። በዚህም ነባሩ ትውፊት ወደ ትውልድ ወግና ሥርዓቱን ሳይለቅ በቅብብል መተላለፍ እንዳለበት የሚሞግቱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።

ለምሳሌ ጅራፍን በርችት መተካት 'የምስጢር ተፋልሶ አለው፤ ማኅበራዊ ገጽታው አይበጅም' የሚሉ ወገኖች አሉ። በሆያ ሆዬ የሚሰሙ ግጥሞች ከግብረ-ገብነት ያፈነገጡ፣ ዓለማዊ መልዕክት ያላቸው፣ ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ ይዘት ያዘሉ ሆነው እንደሚስተዋሉ በመጥቀስ ይህን ተግባር አጥብቀው ይተቻሉ። 

በሌላ በኩል በሙልሙል ዳቦ የተጀመረው እና ሃይማኖታዊ አንድምታ የነበረው የታዳጊዎች 'ሆያ ሆዬ' ትውፊታዊ ሥርዓቱን እየለቀቀ ገንዘብ መሰብሰቢያ መሆን እንደሌለበት ይነሳል። በቡሄ ምሽት በከተሞች አካባቢ የሚስተዋል የመጠጥና ስካር ድባብም እንዲሁ። ይልቁንም ለነዳያን እየዘከሩ እና እየዘመሩ በሰፈር ማኅበራዊ አብሮነት የሚያሳዩ ወጣቶችን ማበረታታት እንደሚገባ ይመክራሉ።

መልካም ቡሄ!!

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም