ቀጥታ፡

የክረምት በጎ ፈቃድና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ሕዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን መለወጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፤ ነሓሴ 13 /2015 (ኢዜአ) :-የክረምት በጎ ፈቃድና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ሕዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን መለወጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑ ተገለፀ።

 የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሚያዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ''የክረምት ትጋት የዓመት ልማት'' በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

ውይይቱም በዋናነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በመድረኩም የውይይት መነሻ ሃሳብ ካቀረቡት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ሕዝብን በማስተባበር በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳት፣ ደም ልገሳና ሌሎች የጤና እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ደግሞ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች በስፋት የተሰማሩባቸው መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህም  በዜጎች መካከል ያለው መቀራረብና አብሮነት እንዲጎለብት አድርጓል ነው ያሉት፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በመተባበር ታላላቅ የልማት ትልሞችን እውን ማድረግ እንደሚችሉ ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በአንድ ጀምበር ከ500 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡


 

የአረንጓዴ አሻር መርሃ-ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በበኩላቸው፤ የአካባቢ መራቆት የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአማካይ በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር ደን እንደሚጨፈጨፍ ጠቅሰው፤ ይህን ተከትሎ በሚከሰት የአፈር መሸርሸር ምክንያት ኢትዮጵያ ከምርትና ምርታማነት በዓመት ማግኘት ከነበረባት 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በደን ልማት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያውያንን የማድረግ አቅም ያሳየ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡


 

የአገር ግንባታ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ኃላፊነት አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ ናቸው፡፡

በመሆኑም የግሉ ሴክተር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡


 

የደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ሰለሞን ክቤ፤ የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የከተማ ግብርና ሥራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ ይህም የትምህርት ቤቱን ማኅበረሰብ የሥራ ባህል በበጎ ጎኑ የቀየረ ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የከተማ ግብርና ሥራውን ከራስ ባለፈ በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች የማስፋት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የአካባቢ ጥበቃና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር ረገድ በጎ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ይተብቱ ሞገስ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን የደን ልማት ጉዞ የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በመርሃ-ግብሩ በአርዓያነት መሳተፋቸው ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ 


 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ የአገር ልማትን ውጤታማ በማድረግ ረገድ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በዘንድሮው ክረምት ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በዘላቂነት ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ይበልጥ በማጎልበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም