መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ በጎ አድርጎት ድርጅት በመቱ ከተማ በ130 ሚሊዮን ብር ማዕከል ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ በጎ አድርጎት ድርጅት በመቱ ከተማ በ130 ሚሊዮን ብር ማዕከል ሊገነባ ነው

መቱ ነሐሴ 13/2015 (ኢዜአ) መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ የበጎ አድራጎት ድርጅት በመቱ ከተማ በ130 ሚሊዮን ብር ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠ።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በመቱ ከተማ ቅርንጫፉ ለአረጋውያኑና ለአዕምሮ ሕሙማኑ ማቆያ የሚሆን ማዕከል በ130 ሚሊዮን ብር ሊገነባ መሆኑን ገልጿል።
በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የክልል ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ማኅተመ በቃሉ፣ በመቱ ከተማ በሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ 50 አረጋውያንንና የአዕምሮ ሕሙማን እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።
ድርጅቱ አሁን በ130 ሚሊዮን ብር ሊያስገነባ ባሰበው ማዕከልም ከኢሉ አባቦር በዞኑና አጎራባች ክልሎች የሚገኙ ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንን እና የአዕምሮ ሕሙማንን ለመንከባከብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም የመንግስት አካላት የማዕከሉን ግንባታ እንዲያግዙና የበጎ አድራጎት ስራውን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግርማ ታረቀኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በቅርበት ያግዛል።
በዚህም የመቱ ከተማ አስተዳደር የበጎ አድርጎት ድርጅቱ ለማዕከል ግንባታና ሌሎች ስራዎች ማከናወኛ የሚሆን መሬት መስጠቱን አስታውሰዋል።
የኢሉ አባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው የበጎ አድራጎት ተግባር ከመልካም ልብ የሚመነጭ በመሆኑ ሁሉም ተባባሪ መሆን አለበት ብለዋል።
በጎዳና የወደቁ አረጋውያንንና የአእምሮ ሕሙማንን በማንሳት ስራ ላይ በተሰማራው ከዚህ በጎ አድራጊ ድርጅት ጎን ሁሉም የዞኑ ህዝብ በሚቻለው ሁሉ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የመቱ ከተማ ነዋሪዎችም ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጎን በመሆን የተቸገሩትን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሸዋዬ በቀለ ''እያንዳንዳችን ነገ ምን ሊገጥመን እንደሚችልና የማን ድጋፍ ሊያስፈልገን እንደሚችል ስለማናውቅ በበጎ ተግባር መሳተፍ አለብን'' ብለዋል።
አቶ ታሪኩ ጌታቸው በበኩላቸው ''ሰውን በሰውነቱ ብቻ በመረዳት ድጋፋችንን ለሚሹ ሁሉ የምንችለውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል'' ነው ያሉት።