መንግስት ለገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ውጤታማነት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀትና የተጠያቂነት አሰራር ማስፈን ይገባዋል - የምጣኔ ኃብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ውጤታማነት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀትና የተጠያቂነት አሰራር ማስፈን ይገባዋል - የምጣኔ ኃብት ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2015 (ኢዜአ) ፡- መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላወጣው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ውጤታማነት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀትና የተጠያቂነት አሰራር ማስፈን እንደሚገባው የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በማርገብ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲሁም የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህም ቁልፍ በሆኑ የወጭ ንግድ ዘርፎች በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታት የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 ቀመር እንዲሻሻል ተደርጓል።
በዚህም መሰረት የሸቀጦች እና የአገልግሎት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶውን ለባንክ፣ ቀሪውን በራሳቸው የባንክ ሂሳብ እንዲያስገቡ መፈቀዱን የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል።
ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ላይ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል ተብሏል።
በያዝነው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ የብድር መጠን ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር 1/3ኛ እንዳይበልጥ ማድረግም ከማሻሻያዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው።
ይህም በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዋጋ ንረቱን ከ20 በመቶ በታች እንዲሁም በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ያለመ ማሻሻያ መሆኑ ተገልጿል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ኢኮኖሚን ለመግራት በየጊዜው በጥናት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የልማት ኢኮኖሚክስ ባለሙያና አማካሪ ደረጀ ደጀኔ እንዳሉት፤ ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግና የዜጎችን ኑሮ ለመለወጥ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ ነው።
ኢኮኖሚውን ለመግራት ትልቅ መሳሪያ የሆኑትን የሞኒተሪ እና ፊስካል ፖሊሲዎች በጥቅል ከማሻሻል ባለፈ በዝርዝር በመመልከት ተከታታይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይፈልጋል ብለዋል።
በዓለም ላይ ዛሬ ባለግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት እንደ ቻይናና ቬትናም ያሉ አገራት ለዚህ የበቁት ቀጣይነት ያለው የፊስካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር የምጣኔ ኃብት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አቡሌ መሀሪ በበኩላቸው የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ በተለይ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የአገር ውስጥ ብድር እድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ መገለጹ ከፍተኛ የሆነ ብድር ወደ ገበያው እየሄደ ከኢንቨስትመንት ይልቅ ቋሚ ሃብት ላይ የሚውለውን ገንዘብ እንደሚቀንሰው ገልጸዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ፖሊሲ ከማሻሻል ባለፈ ገቢራዊ የሚደረግበት የተጠያቂነት አሰራር ሥርዓት ማስፈን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንደ ፍራንኮ ቫሉታ፣ የነዳጅ ድጎማና መሰል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ቢወስድም የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለማምጣታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በጥቁር ገበያ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ምንጩን ማድረቅ፤ ለታማኝና ሀገር ወዳድ ባለሃብቶች ማበረታቻና እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል።
መንግስት ለግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት ከመስጠት ባለፈ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ማዘመን እና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ውጤታማ ለማድረግ መንግስት ተቋማዊ አደረጃጀቱንና የአሰራር ሥርዓቱን ማዘመን እንዳለበት ምሁራኑ ተናግረዋል።
የዋጋ ንረት ብሔራዊ ባንክ ብቻውን ሊቆጣጠረው የሚችል ባለመሆኑ የሌሎች አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።