ቀጥታ፡

በተለያዩ ጊዜያት ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች ለመውጣት በሚያስተሳስሩን ነባር አገራዊ እሴቶቻችን ላይ ማተኮር ይገባል- ምሁራን 

ሃዋሳ ፤ ነሐሴ 13/2015 (ኢዜአ) ፡- በተለያዩ ጊዜያት ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች ለመውጣት በሚያስተሳስሩን ነባር አገራዊ እሴቶቻችን ላይ ማተኮር እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ።

የሰላም ሚኒስቴር፤ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "አገራዊ እሴቶቻችን ለጠንካራ አገር ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በሃዋሳ እየተካሄደ ነው ። 

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የስነ ሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዳኜ ሽብሩ "ነባራዊ ሀገራዊ እሴቶቻችንና ወቅታዊ ሁኔታዎች" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ፣ በሀገራችን የተደቀነውን ችግር ለመፍታት ነባር እሴቶቻችንን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። 

"ታማኝነት፣ መቻቻል፣  መከባበር፣  መረዳዳትና ተጋግዞ የመኖር እሴቶቻችንን ጠንክረው እንዲወጡ ለማድረግ መስራት አለብን" ሲሉ ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ያሉን ነባር አገራዊ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው ምክንያት በርካታ ችግሮች መጋረጣቸውን አመልክተዋል።

"ምን ቸገረኝ፣ ምን አገባኝ ዓይነት ልምዶች እየተንፀባረቁ ነው" ያሉት ዶክተር ዳኜ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ሁሉም ዜጋ ለነባር እሴቶች ትኩረት በመስጠት ሊጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ንጉስ በላይ በበኩላቸው "የሀገር ግንባታና ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳሉት ለአገር ግንባታ ትልቁ መሳሪያ ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው። 

"አገር ሲገነባ አገራዊ ቅንጅት ያስፈልገናል ለዚህ ደግሞ የጋራ ልናደርጋቸው የሚገቡ የጋራ መገለጫዎች ሊኖሩን ይገባል" ብለዋል። 

በነባር ዕሴቶቻችን ውስጥ ያሉትን የመነጋገርና የመደማመጥ ባህሎቻችንን በመጠቀም አንድነታችንን ማጽናት እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና የብዝሃነት ተመራማሪው ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው አብሮ የመኖር እሴቶችን በማጠናከር ችግሮቻችንን መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል። 

ባህላዊ እሴቶቻችን የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፎች መሆናቸውንም ጠቁመው ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወሰን ሳይገድባቸው የሚጋሯቸው በመሆኑ ችግርን ለመቋቋም አቅም ይሰጡናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም