አረንጓዴው ጎርፍ በቡዳፔስት - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴው ጎርፍ በቡዳፔስት
ኢትዮጵያ በ35 አትሌቶች የምትወከልበት 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ይጀመራል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ ከምሽቱ 3 ሰአት ከ55 36 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ‘National Athletics Centre’ ስታዲየም የሚደረገው የ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል።
በውድድሩ ላይ በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ጉዳፍ ፀጋይ፣እጅጋየሁ ታዬ እና ለምለም ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ለተሰንበት እ.አ.አ በ2021 በኔዘርላንድስ ሄንግሎ በተካሄደ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር 29 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ከ3 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በትውልድ ኢትዮጵያ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችውን የአትሌት ሲፋን ሀሰን የዓለም ክብረ ወሰንን በአምስት ሴኮንድ በማሻሻል የክብረ ወሰኑ ባለቤት መሆኗ የሚታወስ ነው።
በውድድሩ ላይ የምትሳተፈው ሌላኛዋ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በሰኔ ወር 2015 በስፔን በተካሄደ ውድድር 29 ደቂቃ ከ29 ሴኮንድ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።
አትሌት ጉዳፍ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ አይዘነጋም።
አትሌት ለምለም ኃይሉ 29 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ15 ሴኮንድ እና አትሌት እጅጋየሁ ታዬ 29 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።
በትውልድ ኢትዮጵያ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ ሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን፣ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቺቤትና በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ካዛኪስታናዊ የሆነቸው አትሌት ካሮሊን ቼፕኮኤች ኪፕኪሩይ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 6 ሰአት ከ35 በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድሩ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ጌትነት ዋለና አብርሃም ስሜ ይሳተፋሉ።
የዓለም አትሌቲክስ አትሌት ለሜቻ በሰኔ ወር 2015 በፓሪስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የጨበጠውን የዓለም ክብረ ወሰን በቅርቡ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።
ከቀኑ 8 ሰአት ከ15 በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣አትሌት ብርቄ ኃየሎምና አትሌት ሂሩት መሻሻ ይሳተፋሉ።
ከምሽቱ 2 ሰአት ከ2 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት አዲሱ ግርማ፣አትሌት ታደሰ ለሚ እና አትሌት ሳሙኤል ዘለቀ ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ1 ሺህ 500፣በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣በ5 ሺህ ሜትር፣በ10 ሺህ ሜትርና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ800 ሜትር በሴት ብቻ እንደምታሳተፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የሻምፒዮናው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ‘National Athletics Centre’ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይከናወናል።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ200 አገራት በላይ የተወጣጡ ከ2 ሺህ በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሻምፒዮናው እስከ ነሐሴ 21/2015 ይቆያል።