የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን የሚያሰፋ ወሳኝ አንድ ነጥብ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን የሚያሰፋ ወሳኝ አንድ ነጥብ አግኝቷል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን የሚያሰፋ ወሳኝ አንድ ነጥብ አሳክቷል።
ንግድ ባንክ በዩጋንዳ በንጄሩ ከተማ ‘FUFA Technical Center Stadium’ ዛሬ ባደረገው ሶስተኛ የማጣሪያ ጨዋታ ከዩጋንዳውን ካምፓላ ኩዊንስ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዋ ሎዛ አበራ ያስቆጠረችው ግብ ንግድ ባንክን ቀዳሚ አድርጋ የነበረ ቢሆንም ዛይና ናንዴዴ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ሰአት ያስቆጠረችው ግብ ካምፓላ ኩዊንስን አቻ አድርጋለች።
ውጤቱን ተከትሎ በምድብ አንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ነጥቡን ወደ 7 ከፍ በማድረግ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ነሐሴ 18/2015 ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ጋር ያደርጋል።
የንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በመጨረሻ ጨዋታው አቻ ካወጣ ወይም ካሸነፈ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉን ያረጋግጣል።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የብሩብዲውን ቡጃ ኩዊንስን 2 ለ 1 እንዲሁም የጅቡቲውን ፋድ ክለብ 8 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በምድብ አንድ በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ የደቡብ ሱዳን ዬ ጆይንት ስታርስ የጅቡቲውን ፋድ ክለብ 2 ለ 0 አሸንፏል።