ቀጥታ፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል-የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2015(ኢዜአ)፦ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ማረጋገጡን አስታወቀ። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ተመልክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጎብኝተዋል።

የቦርዱ አባላት ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ የሚገናኙበት፣ ከጠበቃዎቻቸው ጋር የሚማከሩበት እና የቃል መቀበያ ክፍሎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ጉብኝቱን ተከትሎም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴ ጋር ተወያይተዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራ አንደሞ በዚህ ወቅት፥ ከተጠርጣሪዎች ጋር ስላለው ሰብአዊ መብት አያያዝ ውይይት በማድረግ መረጃ መሰብሰባቸውን ገልጸው ውይይቱ በተጠርጣሪዎቹ ፍላጎት መሰረት መገናኛ ብዙሃን በሌሉበት በዝግ መካሄዱን ተናግረዋል።

በጉብኝታቸውም ተጠርጣሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ መልካም መሆኑን፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ የሚገናኙበት ሁኔታ መኖሩን፣ ምቹ የማረፊያ ክፍሎች እንደተዘጋጁላቸው፣ የቃል መቀበያ ክፍሎች ንጹህና ሂደቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ተጠርጣሪዎቹ አካላዊ ሁኔታቸው ጤናማ መሆኑንና ሰብዓዊ መብት አያያዛቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል ነው ያሉት።

በቀጣይ ተጠርጣሪዎቹ ምርመራቸው ተጠናቆ በፍጥነት ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው ከቢሮ ጋር መግባባት መደረሱን ጠቅሰዋል።

በማዕከል የተጀመረውን ተጠርጣሪዎችን የመጎብኘት ተግባር በቀጣይ በአማራ ክልልም እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ እንዳሉት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 226 መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉት እና በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መጎብኘቱን ተናግረዋል።

ከቦርዱ ጋርም ተጠርጣሪዎች ስለሚገኙበት ሁኔታና ሰብዓዊ መብት አያያዛቸው እንዲሁም የምርመራ ሂደቱን በሚመለከት ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግና ተጠርጣሪዎችንም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

መርማሪ ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ እስር በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች እየተፈጸመ ነው በሚል የሚነሳ መረጃ እንዳለ የጠቀሱት አቶ አዝመራው፤ ቦርዱ ክትትል አድርጎ መረጃውን ለህዝብ በይፋ እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ህግን መሰረት አድርጎ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ብቻ በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በአዋጁ ስም የትኛውም አካል ሰዎችን ማንገላታትም ሆነ ለእስር መዳረግ እንደማይችልና ፈፅሞ በተገኘ አካል ላይም ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም የፀደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተል መርማሪ ቦርድ ማቋቋሙ ይታወቃል።

መርማሪ ቦርዱም ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጋር ውይይት በማድረግ ስራውን ጀምሯል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም