“አዲስ አበባ” በሞስኮ:- ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ 27 ዓመታት የዘለቀ ጉዞ

 

በአየለ ያረጋል

ጊዜው በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ቀትሯል። ‘ጋርደን ሪንግ’ ጎዳና ማዕከላዊ ሞስኮ ከተማን (የሩስያ ርዕሰ መዲና) እንደ መቀነት ይጠመጠማል። በዚህ ጎዳና ከሚገኝ አንድ ተቋም ለብርቱ ጉዳይ ለመግባት የጎግል ካርታ ተከትዬ ከሜትሮ (ምድር ባቡር) መውጣቴ ነበር። በዚህ ቅጽበት ነበር ‘አዲስ አበባ ሬስቶራንት’ የሚለውን ስፍራ አቅጣጫ በድንገት ያስተዋልኩት። በሞስኮ ጎዳናዎች የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ማግኘት እንደ ምዕራብ ሀገራት ተራ ነገር አይደለም። ብርቅ ነው ማለት ይቀላል። እናም የኢትዮጵያ ሬስቶራንት በድንገት ማግኘቴ ለእኔ ‘ድንገቴ ፈንጠዝያ’ ሆነብኝ። ከሄድኩበት ቢሮ መግባቱን ትቼ በጎግል ካርታ እየተመራሁ ወደ ፊት ገሰገስኩ። ወደ አዲስ አበባ ሬስቶራንት። በ‘ጋርደን ሪንግ’ ጎዳና የአምስት ደቂቃ ርምጃ የጎግል ካርታው ‘ርቀቱ’ ዜሮ ሆነ። ቀና ስል በሀገሬ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የቀለሙ ፊደላት አነበብኩ። የሩስኪ ቋንቋ ፊደላት ቢሆኑም ደጉ ነገር የማውቃቸው ፊደላት ነበሩ። ‘አዲስ አበባ’ ደረስኩ!! (የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞስኮ ቢሮም ከአዲስ አበባ ሬስቶራንት ፊት ለፊት ይገኛል)

ገርበብ ያለውን በር ገፍቼ ገባሁ። ከገባሁ ጀምሮ አዲስ አበባ እንጂ ሌላ ሀገር መሆኑን ዘነጋሁ። የሀበሻ ዘፈን ይደመጣል። ግድግዳው በሀበሻ ስዕላት ተሞልቷል። ጣሪያው በእንስሳት ቆዳ ተጊጧል። ባንኮኒው የብዝሀ-ኢትዮጵያ መልክ ይዟል፤ በቅርጻ ቅርጾች እና አልባሳት ደምቋል።


 

ባንኮኒው ውስጥ ያገኘሁትን ሰው ተዋወቅሁ። ዶክተር ጥላሁን መኮንን ነው-የሬስቶራንቱ ባለቤት። የወገን ወግ ተጨዋወትን-አልፎ አልፎ ወደሩሲያኛ ቋንቋ እየተሰረቀ። በዚህ ቅጽበት ብቻ አይደለም። ሌላም፤ ሌላም ቀን እስከ ሞስኮ ቆይታዬ ድረስ። በመጨረሻም ‘አዲስ አበባ በሞስኮ’ን መጣጥፍ ለመጻፍ ወደድኩ። 

የእህል ውሃ ነገር ሆኖ እዚህ ቦታ ብንገናኝም ጥላሁን መኮንን የተዋጣለት የሚባል ጎበዝ ሙዚቀኛ ነበር-ፒያኒስት!!

ጥላሁን እና ሞስኮ-

ከልጅነት እስከ ዕውቀት

ጥላሁን መኮንን ትውልዱና ዕድገቱ አዲስ አበባ ነው። የሞስኮ እና የጥላሁን ትውውቅ ግን በዕድሜው ማለዳ የተጀመረ ነው። ሞስኮን የረገጠው ገና በለጋነት ዕድሜው ነው። “በ1976 ዓ.ም ሕጻን እያለሁ ሞስኮ መጥቻለሁ። የሙዚቃ ፌስቲቫል ነበር። ስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ይመስለኛል” ይላል። 

ጥላሁን ከልጅነቱ ጀምሮ የሕጻናት ኪነት ቡድን አባል ነበር። በ1978 ዓ.ም የነ ጥላሁን የኪነት ቡድን በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረ ውድድርን በማሸነፍ በቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ለሕፃናት በዓል ተጋበዘ። ጥላሁን እና ሌሎች አራት ጓደኞቹም ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ሞስኮ ተጓዙ። ጥላሁን ለሁለተኛ ጊዜ ሞስኮን ረገጠ ማለት ነው። “በዚህ ወቅት ሚኒስትሪ (የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና) የተፈተንኩት እዚሁ ነበር” ይላል። 

ሙዚቃ የጥላሁን የልጅነቱ የነፍስ ጥሪ ነበረች። በትምህርቱም ቀለሜ ነበር። በብዙ ሙዚቀኞች እንደሚስተዋለው ወላጅ አባቱ የሙዚቃ መክሊቱን እንዳያጣጥም ሳንካ አልሆኑበትም። ከልጅነቱ ጀምሮ አይረሴ የኪነት ትውስታዎችን ሰንቋል። በዘመነ ደርግ የአብዮት ዓመታት በሕጻናት ኪነት ቡድን ውስጥ ትልልቅ ሀገራዊ መድረኮች ላይ ተሳትፏል። ጥላሁን እና ጓደኞቹ በሶማሊያው ዜያድባሬ ወረራ ጊዜ ሰራዊቱን ለማነቃቃት በሚደረጉ መድረኮች፣ በአብዮት በዓላት እና ዓለም አቀፍ በዓላት አከባብር ላይ በሕጻናት ኪነት ውስጥ ዘምሯል። በተለይም በኢሕዴሪ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ፓርቲ ምስረታ ወቅት የብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ እንዲገነዘብ ያስቻለውን ዕድል አግኝቷል።

“አያሌ የአብዮት መዝሙሮችን ዘምረናል። በብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ የሚተላለፍ የኛ መዝሙር ነበር። ለምሳሌ ‘አይዞን ተነሺ ኢትዮጵያ፤ አለን ልጆችሽ’ የሚለው አይረሳኝም። ሁልጊዜ ቅዳሜ፣ ቅዳሜ እንቀረጽ ነበር። ትልልቅ የመንግስት መድረኮች የኛ ኪነት በድኑ ስራዎችን ያቀርባል። 

የዕድገት በሕብረት ዘመቻ መዝሙርና አርማ የተቀበልነው እኛ ነበርን። የሚገርምህ በቅርቡ ስለዕድገት በሕብረት ዘመቻ ታሪክ ሲተረክ የልጅነት ፎቶየን (የስምንት ወይ የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ) በቴሌቪዥን አይቼው ደስ ብሎኛል” ይላል።

ጥላሁን የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቆ በፒያኖ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። ለመመረቂያም ትልቅ ኮንሰርት አዘጋጅቷል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት አስተምሯል። የዛሬው የኢትዮጵያ ሙዘቃ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩን ከተማሪዎቹ መካከል ይጠቅሳል።

ከአስተማሪነቱ ጎን ለጎንም ፒያኖና አኮርዲዮ በመጫወት ብዙ መድረኮች ላይ ይሳተፍ ነበር። ጥላሁን ገሰሰ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ መሀሙድ አህመድ እና መሰል ዝነኛ ድምጻዊያን በተሳተፉበት መድረክ ሙዚቃ ተጫውቷል። የሙዚቃ ቡድን መሪ ሆኖም  ነበር። በሀገር ውስጥ የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በማደራጀትም ተሳትፏል።

ከሁለት ዓመታት የመምህርነት ቆይታ በኋላ ነበር የውጭ ትምህርት ዕድል ያገኘው። በወቅቱ ምሥራቅ ጀርመን፣ ቡልጋሪያ እና ሩስያ ምድቦች ነበሩ። ግርማ ይፍራሸዋ፣ ይገዙ ደስታ፣ መታሰቢያ መላኩና መሰሎቹ በሶስቱ ሀገራት ትምህርት የተማሩበት ዘመን ነው። ጥላሁንም ከአንድ ሺህ ተወዳደሪዎች መካከል በነበረው ውጤት ቀዳሚ ተመራጭ ሆኖ ለሁለተኛ ዲግሪ ሩስያ ተላከ። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህራንም “እናት ሀገርህን እንዳትረሳ አደራ” ብለው ‘የኢትዮጵያ ካርታ’ ሰጥተው ላኩት።

በሞስኮ ሁለተኛ ድግሪውን በከፍተኛ አፈጻጸም (በሀገሪቷ አገላለጽ ቀይ ዲፕሎማ) ይዞ ከመመረቁ ያለምንም ፈተና የሶስተኛ ድግሪ (ዶክትሬት) ትምህርት እንዲቀጥል ዕድል ተመቻቸለት። በኦርኬስትራ መሪነት (ኮንዳክተር) ሙያ ሶስተኛ ዲግሪውን ያዘ። የሩስያ ቋንቋ አስተርጓሚነት ዲፕሎማም ወሰደ። ከሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ኦርኬስትራ ጋር ትልቅ ኮንሰርት አካሄደ።

በሞስኮ ትምህርት ካልቸራል የኒቨርሲቲ መምህርነት ተቀጠረ። “አስተማሪነት በወቅቱ የኑሮ ደረጃው ከባድ ነበር” ይላል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የመንግስት ስርዓት ለውጥ ተደረገ። ታላቋ ሶቬት ሕብረትም ተበታተነች። ፒያኒስቱ ጥላሁን ቀስ በቀስ ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀለ። ‘አዲስ አበባን በሞስኮ’ ከፍቶ ኑሮውን ቀጠለ።

አዲስ አበባ በሞስኮ

አዲስ አበባ ሬስቶራንት በሞስኮ ከተማ ውስጥ በብቸኝነት አለ የሚባል የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ነው። ጥላሁን እንደሚለው ሬስፖራንቱ በቤተሰብ የተጀመረ ነው። ከቤተሰብ ተረክቦ ‘አዲስ አበባ በሚል ስያሜ አስቀጠለው። ዘንድሮ 27 ዓመት አስቆጥሯል።

የሬስቶራንቱ አገልግሎት ከምግብና መጠጥ ሽያጩ ይልቅ የኢትዮጵያን ገጽታ እና ባህል በመሸጥ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ያምናል። የደንበኞቹ ማንነት እና የሚቀርቡ ምግቦች አይነት ይህን ያረጋግጣል።


 

“አዲስ አበባ የሩስያዎች ምግብ ቤት ነው። ደንበኞቻችን የውጭ ዜጐች ናቸው-በአብዛኛው ሩስያዎች። የዲፕሎማቶች ማረፊያ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሩስያዊያን መሰባሰቢያቸው ነው” ይላል። ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱ ቱሪስቶችም ከመሄዳቸው በፊት የኢትዮጵያን ምግብ እና ባህል የሚለማመዱት አዲስ አበባ ሬስቶራንት ነው።

የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለማስለመድ ገጠመኞችንም ያነሳል።“አንድ ቀን እንጀራ ምግብ ታዝዘን እንጀራ ቁርጥ በጎን አቅርብንላቸውና ‘ናፕኪን’ መስሏቸው ነበር። የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ መሆኑን እና እንዴት መበላት እንዳለበት አሳየናቸው። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የገባ ደንበኛ እንጀራ ሳይበላ አይሄድም። ምግቡ ማቀዝቀዣ ውስጥ የገባ ሳይሆን ፍሬሽ ነው። ኬሚካል የለውም። ቡናው ቀጥታ ከኢትዮጵያ እናስመጣለን-የሀረር ቡና። በኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስርዓት ከነ ጭሱ እየተፈላ ይቀርባል። ይህን ይመርጡታል። እንጀራ፣ ስጋ ወጥ፣ የበግ ጥብስ፣ ዶሮ ወጥ… ለምደዋል” ይላል።

ሶቬት ሕብረት ስትፈራርስ ከባድ የፈተና ጊዜ እንደነበር ያነሳል። በርካታ የአፍሪካ ሬስቶራንቶች ቢከፈቱም እንደ አዲስ አበባ መቀጠል ሳይችሉ እንደተዘጉ ያነሳል። ነገር ግን በአውሮፓዊያኑ አቆጣጥር 1998 ጀምሮ ሁሉም ነገር መስመር እየያዘ ስለመምጣቱ ይገልጻል።

አዲስ አበባ ሬስቶራንት በሞስኮ የሚገኙ ሀበሾች ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካዊያን የሚገናኙበት ስፍራ ጭምር ነው። ተጠቃሽ የጥቁሮች ሬስቶራንት ነው። 

“ብዙ የአፍሪካ ሬስቶራንት የለም። የሩስያና የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆን ሚናውን እየተወጣ ነው ማለት እንችላለን። የአፍሪካ ኤምባሲዎች በሬስቶራንቱ ውስጥ ዝግጅት ያደርጋሉ። በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2000 ድረስ ሬስቶራንቶች ነበሩ። አሁን የሉም። እኛ ኢትዮጵያን ብቻ ነን።” 

በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በሬስቶራንቱ ያዘጋጃል። ከኢትዮጵያ ወደ ሞስኮ ያቀኑ እንግዶች (ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ) ወደ አዲስ አበባ ሬስቶራንት ጎራ እንደሚሉ ይገልጻል። 

“ወደ ሩስያ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ሬስቶራንትን ሲያገኙ ይደሰታሉ። በ2018ቱ የዓለም ኦሎምፒክ የመጡ እንገዶች ትልቅ ደስታ ነበራቸው። ብዙዎቹ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ይመጣሉ። ይህም አለ ወይ? ይሉናል። ትንሿ ኢትዮጵያ፣ ትንሿ አዲስ አበባ ይሉናል። በጣም ይደሰታሉ። ያበረታቱናል። ከበሩ ጀምሮ አዲስ አበባ የሚለውን ሲያዩ ይደሰታሉ።”  

በርግጥም በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘኋቸው አፍሪካዊያን ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ መምራን ‘እንጀራ’ እና የኢትዮጵያውያን ‘ውዝዋዜ’ እንደሚያስደስታቸው ገልጸውልኛል። አንዳንዶቹም ከትክሻቸው ወዝወዝ እያሉ ውዝዋዜን በቀልድ መልክ ለማሳየት ሞክረውልኛል። ይህን ያወቁት ‘በሞስኮዋ አዲስ አበባ’ ነው።


 

የሬስቶራንቱ እንግዶች ስለኢትዮጵያ መልካም ዕይታ እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋል። ጥላሁን የኢትዮጵያ ስም እንዲጎድፍ አይፈልግም። የኢትዮጵያ ምግብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነው የሚከፈተው። ሬስቶራንቱ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እንዲሸት እንደሚሰራ ይናገራል። አዲስ አበባሬስቶራንት በሩሲያን መሰል በውጭ ሀገራት የተከፈቱ፣ የኢትዮጵያን ስምና ገጽታ የሚሸጡ፣ የሀገር ባህልና ወግ የሚያስተዋውቁ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ኤምባሲዎች ሊደግፏቸው እንደሚገባ ያምናል።

“ኤምባሲዎችም ሊደግፉን ይገባል። ሬስቶራንቱ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ነው የሚያገለግለው። የኢትዮጵያ በዓል ሲኖር ምግብ ሰርተን እናስደስታለን። ባህላችን እንሸጣለን። ዓላማችን ይህ ነው። ብዙ ሊከታተሉን ይገባል። ኢትዮጵያን እናስተዋውቃለን። ይበልጥ ማስተዋወቅ እና አስፈላጊውን ነገር መደገፍ ይገባል ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያንን ባህል እንሸጣለን። ገፅታዋን እንገነባልን። ኢትዮጵየን ያላዩ እንዲያዩ እናደርጋለን። ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱ ሰዎች መጀመሪያ ስለኢትዮጵያ ባህልና አመጋግብ ይለምዳሉ። ጥናትም ያደርጋሉ።” 

ጥላሁን በሞስኮ ቆይታውና ኑሮው ደስተኛ ነው። ከሙዚቃ ሙያው መነጠሉን እንደ ዕድለ-ቢስነት ቢቆጥርም አዲስ አበባ ሬስቶራንትን ከፍቶ የሀገሩን ስም በማስተዋወቁ ግን ደስተኛ ነው። የሩስያዊያን ባህል እና የህዝቡ ማህበራዊ ውቅር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳስሎሽ መኖሩም ሌላው የሚደሰትበት ጉዳይ ነው።

አሁን የሩስያ ዜግነትም ተቀብሏል። ሁለት ልጆችን ለአካለ መጠን አድርሷል። ሩስያዊያን ስለኢትዮጵያ ያላቸው መልካም ዕይታም ይገርመዋል።


 

“ብዙዎቹ ሩስያዊያን የኢትዮጵያ ወዳጆች ናቸው። ለኢትዮጵያ ያላቸው ወዳጀነትና ቅርበት ሲናገሩ አታምንም። በኢትዮጵያ የነበሩ ወታደሮች ሁሉ ይመጣሉ። ስለኢትዮጵያ ህዝብ ደግነትና የዋህነት ያወሩኛል። አሁን አዲስ አበባ ደርሰው የሚመጡም አሉ። የድሮዋ አዲስ አበባ አይደለችም እያሉ ለውጡን ይተርኩልኛል። የዋህ ናቸው። በባህልም እንመሳሰላለን። ቅዳሜና እሁድ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ እንደ ኢትዮጵያ ሰንበት ይሰማኛል። በጥምቀት በዓል ትዕይንት ልዩ ነው” ይላል። 

ኢትዮጵያና ሩስያ የሚመሳሰል ተከታታይ ስልጣኔ የነበራቸው ታሪካዊ ሀገራት ናቸው። ለብዙ ዘመናትም መልካም ግንኙነት አዳብረዋል። ሩስያ ብዝሀነት ያለባት ሀገር ብትሆንም ከዕድገት እንዳላገዳት ያነሳል። በኢትዮጵያ የሚስተዋለው በጎጥ እና ብሔር እርስ በርስ መናቆር ያሳዝነዋል። ለሀገር ዕድገትና አንድነት ከሩስያ መማር እንደሚገባ ያነሳል። ከምንም በላይ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ባይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም