ቀጥታ፡

በሐረር ከተማ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ይካሄዳል - ቢሮው

ሐረር፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፡-በሐረር ከተማ በ2016 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት እንደሚካሄድ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

ፕሮጀክቶቹ ከተማዋን ውብና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ ነዋሪዎች በአንድ ማዕከል መንግስታዊ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተመላክቷል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም ለኢዜአ እንደገለጹት ሐረር ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ከተማ ብትሆንም የዕድሜዋን ያህል አድጋለች ማለት እይቻልም።

በተለይ ከተማዋን አረንጓዴና ጽዱ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ የተመቸችና ቱሪስቶችን የምትስብ ከተማ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

ለእዚህም የክልሉ ምክር ቤት ከተማዋን ለማልማት "የሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን አዋጅ ቁጥር 160/2014" በማጽደቅ ወደ ሥራ መግባቱንም አክለዋል።  

እንደ ወይዘሮ አሚና ገለጻ ዘንድሮ በከተማው ይገነባሉ ተብሎ ከታቀዱት መካከል የመንግሥት ተቋማት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ሕንጻ ግንባታ ይገኝበታል።



 

በከተማዋ ቀበሌ 14 ልዩ ስሙ ቡቴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባው ዘመናዊ ባለ 18 ወለል ህንጻ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ኃላፊዋ አመልክተዋል።

ህንጻው ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የከተማውን ውበት ከመጨመር ባለፈ፤ በአሁኑ ወቅት  በክልሉ ህንጻ ተከራይተው አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት ተቋማትን የኪራይ ወጪን እንደሚያስቀር አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም ተገልጋዩ ህብረተሰብ በአንድ ማዕከል አገልግሎት በማግኘት በተለያዩ ቢሮዎች በመመላለስ  ለመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ ማነቆዎችን ያቃልላል ብለዋል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ በከተማው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን በጀት የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንደሚከናወን ነው ወይዘሮ አሚና የተናገሩት።

በተለምዶ ከአጂፕ እስከ ደከር ሰላም አደባባይ ድረስ የሚገነባው መንገድ 30 ሜትር ስፋት ያለውና ተሽከርካሪን በሁለት አቅጣጫ የሚያስተላለፍ ከመሆኑም በላይ፤ የእግረኛ መንገድና የመንገድ መብራትን አካቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ግንባታውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ኃላፊዋ ገልጸዋል።


 

መንገዱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ ከሐረር ከተማ ወደ ሶማሌ ክልል የሚከናወነውን የትራፊክ ፍሰት እንደሚያቀላጥፍም ተናግረዋል።  

በተጨማሪም በከተማዋ መግቢያ ከአማሬሳ እስከ አራተኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዋና መንገድ ዳርቻዎችን መልሶ የማልማትና ደረጃ ከፍ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ይህም በተለይ በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ የሚከናወነውን ልማት ለማጎልበት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በመልሶ ማልማት ሥራው ላይ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ኃላፊዋ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም