ቀጥታ፡

ኦቪድ ግሩፕ ለዳያስፖራው 5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ሊያቀርብ ነው 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፡-ኦቪድ ግሩፕ 5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገንብቶ ለዳያስፖራው ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ጋር ተፈራረመ።

የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሥራ ስምምነት የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ሰብሳቢ ቅድስት ልዑል-ሰገድ ተፈራርመዋል።

በዚሁ ወቅት የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ፤ ኩባንያቸው አዲስ የግንባታ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በቤት ልማት ግንባታ ዘርፍ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ችግር እየሆነ የመጣውን የቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል በመንግስት ትብብር ባለፉት አምስት ዓመታት በቤት ልማት ዘርፍ የበኩን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቅርቡም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የስራ ስምምነት በማድረግ በግልና በመንግስት ልማት ፕሮጀክት በ70/30 ሞዴል 60 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ግሩፑ 5ሺህ ቤቶችን ገንብቶ ለዳያስፖራው ለሽያጭ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መቀመጡን ጠቁመው፤ በቅርቡም የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በሚጠቀማቸው የግንባታ ግብዓት አስተማማኝነትና ቅንጅታዊ የአሰራር ሰንሰለትም ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ እንደሚያስችለው አብራርተዋል።

በቀጣይም የግንባታውን ዘርፍ በገንዘብ ለመደገፍ የ"ሞርጌጅ ባንክ" ለመክፈት እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ባንኩ ወደስራ ሲገባም የድርጅታቸውን የመፈጸም አቅም እንደሚያሳድገው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ሰብሳቢ ቅድስት ልዑል-ሰገድ፤ ማህበሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የቤት ፍላጎት ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኦቪድ ግሩፕ ጋር የተደረገው የቤት ግንባታ ስምምነትም 5ሺህ ቤቶችን በማስገንባት የዳያስፖራውን የቤት ችግር ለመፍታ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ልማት ዘርፍ አዲስ ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራን እያከናወነ የሚገኝ አገር በቀል ድርጅት ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም