አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የምታከናውነውን ስራ የበለጸጉ ሀገራት በገንዘብ መደገፍ ይኖርባቸዋል - ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የምታከናውነውን ስራ የበለጸጉ ሀገራት በገንዘብ መደገፍ ይኖርባቸዋል - ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፡- አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የምታከናውነውን ስራ የበለጸጉ ሀገራት በፋይናንስ መደገፍ እንዳለባቸው የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ የኢንዱስትሪና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር ገለጹ።
19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ "የአፍሪካን የአካባቢ ችግሮች ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፣ ትብብርን ማጎልበት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ የኢንዱስትሪና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የኮፕ-28 ፕሬዝዳንት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃብር እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አለምን ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በሚደረገው ሂደት የፋይናንስ አቅርቦት፣ ተደራሽነትና ተመጣጣኝነት መጓደል ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነም ገልጸዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ የሚገኘውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ደግሞ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት በመዘርጋት ውጤታማ ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የበካይ ጋዝ ልቀት ድርሻ ከሰባት በመቶ በታች ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ገፈት ቀማሽ መሆኗ ግን አይቀሬ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የበለጸጉ አገራት የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ የአህጉሪቱን የታዳሽ ኃይል ልማት በገንዘብ መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአፍሪካ አካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ-ግብር የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ፤ ምቹ የግብርና ስራ በመፍጠር የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።
ከበካይ ጋዝ ነፃ የሆነ የኃይል ሽግግር በማድረግ ለአየር ንብረት ምቹ የሆነ ምህዳርን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የምታደርገው ጥረት ለቀሪው ዓለም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለታዳሽ የኃይል አማራጭ ትኩረት በመስጠት የሚያደርጉት ስራ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 19ኛው የአፍሪካ ሚኒስትሮች የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተለያዩ የመፍትሔ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።