የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ሊያመርት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ሊያመርት ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፡-የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አየር መንገዱ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ማምረት እንዲችል የስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓት አከናውነዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳና የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ናቸው።
አየር መንገዱ መንገደኞችን ከማጓጓዝ አልፎ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰማራቱና ይህ ኢንቨስትመንትም መሳካቱ አስደሳች መሆኑን አቶ አክሊሉ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ስምምነቱ ድርጅቱ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ኢትዮጵያ ውስጥ እያመረተ ለአውሮፕላን አምራቾች በማቅረብ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምዕራፍ 2 ከ810 ሚሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አራት ሄክታር የለማ መሬት በመውሰድ የተለያዩ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ለቦይንግ፣ ለኤርባስ እና ጣሊያን አገር ለሚገኝ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ እንደሚያቀርብ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።