ንግድ ቢሮ በሌብነት እና በብልሹ አስራር ላይ በተሳተፉ 222 አመራርና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ወስዷል - ኢዜአ አማርኛ
ንግድ ቢሮ በሌብነት እና በብልሹ አስራር ላይ በተሳተፉ 222 አመራርና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ወስዷል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሌብነት እና ብልሹ አስራር ላይ ተሳትፈዋል ባላቸው 222 አመራር እና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
መጪውን የ2016 ዘመን መለወጫ በዓል የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና 2016 በጀት አመት እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በቢሮው የንግድና ግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ቢሮው አበረታች ስራዎችን አከናውኗል።
የአትክልት ፍራፍሬና የሰብል ምርቶች ማቅረብ የሚያስችሉ የእህል ገበያ ማዕከላት ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ የቁም እንስሳት መገበያያ ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከ450 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነጋዴዎች ቀልጣፋ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደቻለም ነው ያነሱት።
በህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግና መሰረታዊ ሸቀጦችን በፍትሃዊነት ለማህበረሰቡ በማዳረስ በኩል ክፍተት እንደነበር ገልፀዋል።
ቢሮው በበጀት ዓመቱ በሌብነት እና ብልሹ አስራር ላይ ተሳትፈዋል ባላቸው 222 አመራር እና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም አስታውቀዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው ህገ- ወጥ የመሰረታዊ ሸቀጦች ስርጭት ያካሄዱ፣ እጅ መንሻ ሲቀበሉ የተያዙ፣ የመንግስት ስራ ሰዓት ለግል ጥቅም ያዋሉ፣ መስፈርቶችን ሳያሟሉ የንግድ ምዝገባ ፍቃድ ሲሰጡ የተገኙና ደንበኞችን ያጉላሉ እንደሆኑ ነው የተገለፀው።
ሀላፊው አያይዘውም ቢሮው ከመጪው የዘመን መለወጫ በዓል ጋር በተያያዘ በከተማዋ የምርት እጥረት እንዳይከሰት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቁም እንስሳት፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ የአትክትልና ፍራፍሬ እና የሰብል ምርቶች በስፋት ለማቅረብ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው የምርት አቅርቦትን ከማሳደግ በተጨማሪ በምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ በመጋዘን ምርቶችን በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።