ቀጥታ፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ክፍያዎችን በዲጂታል አማራጮች መፈፀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ) ፦ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሁሉንም የአገልግሎት ክፍያዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ አማራጮች መፈፀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ የተፈራረሙት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳህላክ ይገዙ ናቸው፡፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ስምምነቱ ተቋሙም ሆነ ደንበኞቹ የባንኩ ዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ክፍያቸውን መፈጸም ያስችላቸዋል።

ይህም የደንበኞችን ግዜና ጉልበት መቆጠብ ያስችላል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክውም ወደ ተቋማቸው የሚመጡ ተገልጋዮች ከዛሬ ጀምሮ ለሚፈፅሙት የአገልግሎት ክፍያዎች የባንኩን የዲጂታል አማራጮች መጠቀም እንደሚችሉም አብስረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳህላክ ይገዙ በበኩላቸው ስምምቱ ሁሉም የተቋሙ ደንበኞች በሲቢኢ ብርና በሞባይል ባንኪንግ እንዲሁም በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች በአጭር ግዜ ውስጥ የአገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም