ሀገራዊ የቢዝነስ ፖርታልን ወደ አዳማ ከተማ የማስፋፋት ሥራ መጀመሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የቢዝነስ ፖርታልን ወደ አዳማ ከተማ የማስፋፋት ሥራ መጀመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነው የንግድ ስራ ቅልጥፍና ፕሮጀክት የትግበራ መርኃ-ግብር በአዳማ ከተማ መካሄዱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት ሀገራዊ ቢዝነስ ፖርታል መንግስት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ቀላልና ቀልጣፋ ከማድረግ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በንግድ ስራ ቅልጥፍና ያላትን ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያግዛል።
የቢዝነስ ፖርታሉ ሳይቆራረጥ ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጥ የአዳማ ከተማ አስተዳደር በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የሀገራዊ ፖርታል ፕሮጀክት በከተማዋ "ዲጂታል አዳማ" በሚል የተጀመሩትን የዲጂታል አገልግሎት በማፋጠን የከተማዋ ነዋሪዎች ቀላል እና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
የንግድ ስራ ቅልጥፍና ፕሮጀክት ዜጎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኦንላይን አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።
በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው የንግድ ስራ ቅልጥፍና ፕሮጀክት በተመረጡ የኢትዮጵያ ከተሞች ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች በቀጣይ እንደሚሰሩ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።