በምስራቅ ሸዋ ዞን በአሳማ እርባታ የተሰማሩ አርሶ አደር ውጤታማ መሆናቸውን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን በአሳማ እርባታ የተሰማሩ አርሶ አደር ውጤታማ መሆናቸውን ገለፁ
አዳማ፣ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ):- በምስራቅ ሸዋ ዞን በአሳማ እርባታ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደር ውጤታማ መሆናቸውን ገለፁ።
በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ ከ3ሺህ 500 በላይ አሳማዎችን ለርቢ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ነው።
በዞኑ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ማምሪኮ ገለቶ እንደገለፁት ከዝዋይ የአሳማ እርባታ ማዕከል አንድ አሳማ በ4ሺህ ብር በመግዛት ወደ እርባታ ስራ መግባታቸውን ያነሳሉ።
እርባታውን በመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ መጀመራቸውን የሚገልጹት አርሶ አደር ማምሪኮ፤ በአንድ አሳማ በሙከራ ደረጃ የጀመሩት ስራ አስፍተው በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
170 አሳማዎችን ለገበያ ማቅረባቸውን ያነሱት ወይዘሯ፤ አሁንም ለሽያጭ የደረሱ 160 አሳማዎች እንዳላቸው ተናግረዋል።
ለሽያጭ የደረሱ አሳማዎችን በመጪው ጥቅምት ለገበያ እንደሚያቀርቡ የገለፁት አርሶ አደሯ፤ እርባታውን አሁን በእጃቸው ባሉት አሳማዎች ላይ ጨምረው ወደ 600 ለማድረስ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
እርባታውን እያከናወኑ ያሉትም በመኖሪያ ቄያቸው መሆኑን የገለፁት አርሶ አደር ማምሪኮ፤ የእርባታ ቦታ ጥበት ትልቅ ችግር እንደሆነባቸውና ችግሩ እንዲፈታላቸው ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው በተያዘው የበጀት ዓመት የአሳማ እርባታውን ለማስፋት ከ3ሺህ 500 በላይ የሚሆኑትን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
"በዞኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ የአሳማ እርባታ አይታወቅም" ያሉት ሃላፊው፤ አርሶ አደሩ ከዳልጋ ከብት፣ ከበጎችና ፍየሎች እርባታ በተጓዳኝ በአሳማ እርባታ እንዲሰማራና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
''አብዛኛው የዞኑ ወረዳዎች ቆላማና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ ለአሳማ እርባታ አመች የሆነ የአየር ጠባይ ነው'' ያሉት አቶ መስፍን፣ በአሁኑ ወቅት 250 የርቢ አሳማዎችን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም 3ሺህ 500 አሳማዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ በአያያዝና እንክብካቤው ላይ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባለፈ የእርባታ ቦታ ማስፋፊያ ችግሮችን ለመቅረፍና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።