በህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተሳተፉ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተሳተፉ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ድርጅት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ኦፕሬሽን በህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ላይ በተሳተፉ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ከህብረተሰቡ በመጣ ጥቆማ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መጠጥ (ውስኪ) ቤቶች በተደረጉ ጥናቶችና ጥናቶቹን መሰረት ተደርገው በተከናወኑ የኦፕሬሽን ተግባራት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን ነው ፖሊስ የገለጸው።
ውስኪ ቤቶቹ በህጋዊ የንግድ ሽፋን ስም ህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበርም ማረጋገጡንም ገልጿል።
በአጠቃላይ በአስራ አንድ ቤቶች በተከናወኑ የጥናትና የኦፕሬሽን ስራዎች በአምስቱ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የአስራ አምስት ሀገራት ገንዘቦች ከነ ተጠርጣሪዎቹ መያዙን ነው ያመላከተው፡፡
ከተያዙት ገንዘቦችም ውስጥ 2 ሚሊዮን 916 ሺህ 800 የኢትዮጵያ ብር፣ 54 ሺህ 181 የአሜሪካ ዶላር፣ 34 ሺህ 50 ዩሮ፣ 305 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 7 ሺህ 719 የሳውዲ ሪያል፣ 11 ሺህ 440 ድርሀም፣ 52 ሺህ የሊባኖስ ፓውንድ፣ 80 ሺህ 640 የሱዳን ፓውንድ እንዲሁም የተለያዩ ስድስት ሀገራት የገንዘብ ኖቶች መያዙንም ገልጿል፡፡
በህጋዊ የንግድ ስራ ሽፋን ተሰማርተው መሰል የወንጀል ተግባራት ውስጥ የሚገቡ የንግድ ተቋማት ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡