ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ ጋዝ ያከናውናል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በዩጋንዳ በንጄሩ ከተማ ‘FUFA Technical Center Stadium’ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይካሄዳል።

በምድብ አንድ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ እስከ አሁን በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የብሩንዲውን ቡጃ ኩዊንስን 2 ለ 1 እንዲሁም የጅቡቲውን ፋድ ክለብ 8 ለ 0 አሸንፏል።

ምድቡንም በስድስት ነጥብና በዘጠኝ የግብ ክፍያ በመምራት ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ካምፓላ ኩዊንስ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።

በምድብ አንድ ሌላኛው መርሐ-ግብር የጅቡቲው ፋድ ክለብ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ከቀኑ 7 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ከነሐሴ 6/2015 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የማጣሪያ ውድድር እስከ ነሐሴ 24/2015 ይቆያል።

የውድድሩ አሸናፊ ክለብ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በኮትዲቯር አቢጃን በሕዳር ወር 2016 በሚካሄደው ሶስተኛው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም