ቅዱስ ጊዮርጊስ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ቅዱስ ጊዮርጊስ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2015 (ኢዜአ)፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከዛንዚባሩ ኬምኬም ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰአት በታንዛንያ አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ይከናወናል።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለጨዋታው የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ጨዋታውን በሚያደርግበት ሜዳ አከናውኗል።
የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጅታቸውን ከሐምሌ 24/2015 ጀምሮ ቢሾፍቱ በሚገኘው የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚና እና በአበበ በቂላ ስታዲየም አድርገዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
የ2022/23 የዛንዚባር ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ኬምኬም ለጨዋታው ዝግጅቱን በታንዛንያ ሲያደርግ ቆይቷል።
ኬንያዊው ብሮኪ ኢልጃህ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
ክለቦቹ የመልስ ጨዋታቸውን ነሐሴ 21/2015 በአበበ በቂላ ስታዲየም የሚያደርጉ ሲሆን የደርሶ መልስ አሸናፊው ክለብ በቀጣዩ ዙር የ11 ጊዜ የውድድሩን አሸናፊ የግብጹን አል አህሊ ይገጥማል።