ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 11/2015 (ኢዜአ) ፡- ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ የሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ "የአፍሪካን የአካባቢ ችግሮች ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፣ ትብብርን ማጎልበት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው የአፍሪካ አገራት የአካባቢ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአካባቢ ጥበቃ ተወካዮች እና የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የመሬት መራቆት፣ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋና በረሃማነትን አስከትሏል።
ይህም አፍሪካውያንን ለማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች መዳረጉን ጠቁመው፤ በተለይም በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሂደት ላይ ትልቅ ጫና መፍጠሩን ነው አጽንዖት የሰጡት።
አህጉሪቱ የ2033 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ለመከላከል በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በዜጎቿ ተሳትፎ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርኃ-ግብር በመቅረጽ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እያጠናከረች መሆኗን ጠቅሰዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለወጥ የተጋላጭነት አደጋ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ቀርፃ እየተገበረች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግ ተፅዕኖን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓት እየገነባች መሆኑንም እንዲሁ።
በመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ የምድርን ደህንነት ማስጠበቅ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀው በካይ ጋዝ ውስጥ ያላት ድርሻ ከሰባት በመቶ በታች መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም የበለጠ ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
ለዚህም የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ረዳት ዋና ፀሐፊ ኤልዛቤት ማሩማ፤ በዓለም በየዓመቱ 430 ሚሊዮን ቶን የፕላስቲክ ምርቶች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ አፍሪካ የራሷን የፕላስቲክ አወጋገድ የመፍትሔ ስርዓትን በመከተል በዜጎቿ፣ በወንዞቿ እና በስነ-ምህዳሯ ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ መቀነስ ይኖርባታል ብለዋል።
ከነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ በነገው ዕለት የተለያዩ የመፍትሔ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።