በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህግና ስርዓት አክብረን እንሰራለን - በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህግና ስርዓት አክብረን እንሰራለን - በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 11/2015 (ኢዜአ) ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህግና ስርዓት አክብረው እንደሚሰሩ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ገለጹ።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በደብረ ብርሃን ከተማ የታየውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር ተወያይቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ ሰላም መመለሱና የባለ ሦስት እግር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ወደ ስራ መመለሳቸው ለራሳቸውም ለህብረተሰቡም ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን የአዲስ ባጃጅ ባለንብረቶች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሌብ ደመቀ፤ በከተማዋ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ስራ ማቆማቸው ትልቅ ጫና ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሰላም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሰረት ነው ያሉት አቶ ካሌብ፤ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት።
የባጃጅ አሽከርካሪዎች በህገ-ወጥ ተግባራት ከመሳተፍ ታቅበው ህግን ባከበረ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ማህበሩም በባጃጆች አማካይነት የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይኖሩ በመከላከልና ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆኑት አቶ መኮንን አካሉ በበኩላቸው፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ መነሳቱ ሁላችንም ለሰላም ዋጋ እንድንሰጥና በስራችን ላይ ብቻ እንድናተኩር እድል የሰጠ ነው ብለዋል።
በከተማዋ የመጣውን ሰላም መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ህገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥና ከህግ አስከባሪዎች ጋር በመተባባር ሰላምን በማጽናት ሂደት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባል አቶ በድሉ ውብእሸት፤ በከተማዋ ህብረተሰቡና አገልግሎት ሰጪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተግባራዊነቱ እንዲሰሩ ለማድረግ ተከታታይ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በተወሰዱ እርምጃዎች ከተማዋ ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለሷን ጠቅሰው፤ በዚህም ትራንስፖርትን ጨምሮ አገልግሎቶች በመደበኛነት ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
የባጃጅ ትራንስፖርትም ከትናንት ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፤ ሆኖም በባጃጅ ዝርፊያ መፈጸም፣ ታርጋ ሳይለጥፉ መንቀሳቀስ እና ሌሎች ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋ ከ3 ሺህ 500 በላይ ባጃጆች መኖራቸውን ገልጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በባጃጅ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የህግ ማስከበር እርምጃዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የባጃጅ አገልግሎት ሰጪዎችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችንና መደበኛ የትራንስፖርት ህግና ስርዓት አክብረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።