ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ከስምምነቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት ዶክተር እንዳለ፤ ኢዜአ የሚድያውን ዘርፍ ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ጠቀሜታ የሚለካው ለህዝብ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የኢዜአ ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በመልካም አስተዳደር ጉዳዮችና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም የመረጃ ልውውጥን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ተቋሙ ለሀገርና ለህዝብ ይበልጥ ጠቃሚ የሆኑ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ጋር የተደረገው ስምምነትም የመረጃ እጥረትን በማቃለል የተሳካ የመረጃና ኮሙንኬሽን ስራ ለማከናወን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተቋማት ግንባታ ስራዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጠንካራ ከሚባሉት የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም