ቀጥታ፡

ግንባታው የተንጓተተው የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ መንገድ የመጀመሪያው አስፋልት ንጣፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 11/2015 (ኢዜአ)፡-ግንባታው የተጓተተው የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ መንገድ የመጀመሪያው አስፋልት ንጣፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ገለጸ። 

የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ነበር በ2010 ዓ.ም ከቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ /ሲሲሲሲ/ እና  የማማከሩን ሥራ ከሚሰራው ኢንጂነር ዘውዴ አማካሪ ድርጅት ጋር የ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የኮንትራት ውል የተፈጸመው።  

ይሁንና የመንገድ ግንባታው በቻይና ኤግዚም ባንክ ለኮንትራክተሩ ቀሪ 50 በመቶ ገንዘብ ባለመልቀቁና ከወሰን ማስከበር ችግሮች ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ ተጓቷል።  

መንገዱ መጓተቱ በኅብረተሰቡ፣ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። 

መንገዱ መጓተቱ በበጋ ወራት ለአቧራ ብናኝ፣ በክረምት ለጭቃ፣ ለትራፊክ መንገድ መጨናነቅ፣ ለተሽከርካሪዎች ነዳጅ ብክነትና ብልሽት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረው ቅሬታ አቅራቢዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

ችግሩን እንዲፈታም ኢዜአ በተደጋጋሚ የዘገባ ሥራ መሥራቱ ይታወሳል።     

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግንባታውን 50 በመቶ ቀሪ ክፍያውን ከተማ አስተዳደሩ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በመክፈሉ ግንባታው መፋጠኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ኢያሱ ሰለሞን ተናግረዋል። 

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ መንገድ የመጀመሪያው አስፋልት ንጣፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። 

አሁን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ሥራው እየተከናወነ ያለው ይኸው መንገድ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ወደ 50 ሜትር የጎን ስፋት እንዳለውም ገልፀዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በሦስት ቦታዎች ላይ ትላልቅ የትራፊክ ማሳለጫ ረዣዥም ተሻጋሪ ድልድዮች ግንባታን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የመንገዱ ግንባታ 68 በመቶ መድረሱን ገልጸው፤ በቀጣይ የክረምቱ ዝናብ እንደተጠናቀቀ በአጭር ጊዜ ለመጨረስ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

መንገዱ ለከተማዋ የገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጥበት ዋነኛ ቦታ በመሆኑ ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ በተለያዩ አካባቢዎች መንገዶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተለይም የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው በከተማው መካከለኛው ክፍል ላይ የማሳለጫ ድልድዮች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 

ለአብነትም በቦሌና በለቡ አካባቢዎች ላይ ግንባታዎች በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት መሆኑንና ቀሪ ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም