በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 11/2015 (ኢዜአ)፡-በ2015 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
በባለስልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ አደፍርስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለቅመማ ቅመም ልማት ትኩረት ተሰጥቶታል።
በዚህም በቋሚና ዓመታዊ ሰብል 443 ሺህ 859 ሄክታር መሬት በማልማት ከ790 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የተገኘው ምርት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ75 ሺህ ቶን ብልጫ እንዳለውም ነው የጠቀሱት።
በበጀት ዓመቱ ከተመረተው ውስጥ 6 ሺህ 693 ቶን ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ በማቅረብ 11 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ምርቷን ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ህንድ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ አውሮፓ እና ሌሎች መዳረሻ ሀገራት መላኳንም ነው የገለጹት፡፡
በተያዘው የ2016 በጀት ዓመትም 9 ሺህ 342 ቶን ቅምማ ቅመም ወደ ውጭ በመላክ፤ ከ16 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ግብ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
የቅመማ ቅመም ምርታማነትን ለማሳደግም ከዘር ዝግጅት እስከ ምርት አያያዝ ድረስ ያለው ሂደት የሚመራበት መመሪያና የቴክኖሎጂ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ቅመማ ቅመም በኢትዮጵያ በዋነኝነት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በስፋት እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቅመማ ቅመም ግብርና ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡