ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከ984 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚሆን ቦሎቄና ሰሊጥ እየለማ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 11/2015(ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ከ984 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚሆን ቦሎቄና ሰሊጥ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ከምግብ እህል በተጓዳኝ ወደ ወጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ልማት ላይም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ።

በተለይም ቦሎቄ፣ ሰሊጥና ሱፍን ጨምሮ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ትኩረት ከተሰጣቸው የሰብል ዓይነቶች ናቸው ብለዋል።


 

በተያዘው የመኽር እርሻም በክልሉ 984 ሺህ 907 ሄክታር በቦሎቄ፣ በሰሊጥና ሱፍ ሰብል መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህም ቦሎቄ 657ሺህ 664 ሄክታር፣ ሰሊጥ 294 ሺህ 244 ሄክታር እንዲሁም ሱፍ 32ሺህ 999 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል።

ከምግብ እህል ልማት በተጓዳኝ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችንም ለማሳደግ ክልሉ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላይ የተለያዩ ኢንሼቲቮችንና ፓኬጆችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ሙስጠፋ፤ በዚህም የተሻለ ውጤት እያገኘን ነው ብለዋል።

የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ልማት በሁሉም የክልሉ ዞኖች እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የመኸር እርሻ ልማቱን የዘር ጊዜ ወደ ማጠናቀቅ እየተቃረብን እንገኛለን ብለዋል።

በዚህም ከዘርፉ ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጨምረው ገልጸዋል።


 

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ75ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቦሎቄና ሰሊጥን ጨምሮ በተለያዩ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች መሸፈኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ናቸው።

በዚህም ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ እየተመረተ ያለ ቦሎቄ በ70ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን አክለዋል።

ለውጭ ገበያ የሚሆኑ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት ጥራትና ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲመረት አርሶ አደሩን ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በኩታ ገጠም በማደራጀት ተመሳሳይ ምርጥ ዘር፣ ቴክኖሎጂና የምርት ማሳደግያ ግብዓት እንዲጠቀም መደረጉን አመልክተዋል።

በቦሎቄ ልማት ላይ እየተሳተፉ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳው አቶ ወርቁ ኤዳኦ እንዳሉት 13 አባላት ሆነው በ189 ሄክታር መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚሆን ቦሎቄ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመሳሳይ የምርት ማሳደጊያ ግብዓትና የኤክስቴንሽን ድጋፍ ተጠቅመው በሜካናይዜሽን መዝራታቸውን የገለፁት አርሶ አደር ወርቁ፤ በአሁኑ ወቅት ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም