አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ ሆኖ ምክክሩን በፍጥነት በመጀመር ሀገራዊ ግቡን እንዲመታ አበክሮ ሊሰራ ይገባል- ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ ሆኖ ምክክሩን በፍጥነት በመጀመር ሀገራዊ ግቡን እንዲመታ አበክሮ ሊሰራ ይገባል- ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 10/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ ሆኖ ምክክሩን በፍጥነት በመጀመር ሀገራዊ ግቡን እንዲመታ አበክሮ እንዲሰራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
ኮሚሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ስራዎች የተመለከተ የአፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ እስከ አሁን በአምስት ክልሎች የአገራዊ አጀንዳዎች እና የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
የመጀመሪያ ዙር ስራውን በማጠናቀቅ በሌሎች ክልሎች በቀጣይ ዙር የአጀንዳና የምክክሩ ተሳታፊዎች የመለየት ስራ እንደሚያከናውን አመልክተዋል።
የፀጥታ ችግርና የሎጅስቲክስ መጓተት ኮሚሽኑ ስራዎቹን በሚፈለገው መልኩ ለማከናወን እንዳላስቻለው ተናግረዋል።
የኮሚሽኑን ስራዎች ለሕዝቡ ለማስተዋወቅና ምክክሩን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያ ተደራሽነት ችግር እንቅፋት እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን ችግሩን ለመፍታት ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ኮሚሽኑ አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ ሆኖ ምክክሩን በፍጥነት በመጀመር አገራዊ ግቡን እንዲመታ የኮሚሽኑ አመራሮች አበክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉትን በርካታ ስራዎች ለሕዝብ በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ አደረጃጀቱን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
የኮሚሽኑ ስራዎች በሚዲያ በኩል ለሁሉም የማህበረሰብ የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለ ተደራሽ እንዲሆን ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሚዲያን ተጠቅሞ የኮሚሽኑን ስራዎች እና መልዕክቶች ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ የሚያደርገው አገራዊ ምክክር ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።