ቀጥታ፡

የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን ገለጹ

ደሴ ፤ ነሐሴ 10/2015(ኢዜአ)፦ የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የምስራቅ አማራ ሪጅን ኮማንድ ፖስት ከደሴ ከተማ ነጋዴዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መክሯል።


 

በውይይቱ ላይ የደሴ ከተማ ነጋዴዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ከከተማዋ ነጋዴዎች መካከል በሕንጻ መሳሪያ ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ መሃመድ አራጋው እንዳሉት ሕዝብ በጥቃቅን ጉዳዮች በመከፋፈል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶች ዛሬም አላረፉም።

የአባቶቻችንን የአንድነትና የሰላም እሴት ጠብቀን በማቆየት ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም መስራት አለብን ያሉት አቶ መሃመድ አራጋው  አብሮነትን በማጎልበት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማፅናት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።  


 

"ካለፈው ውድመት ሳናገግም ዳግም እንዲህ አይነት ስጋት መፈጠሩ አሳዛኝ ነው" ያሉት አቶ መሐመድ ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍም ሆነ ቤተሰብ መምራት ስለማይቻል ለሰላም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

"የአካባቢያችንን ሰላም በጋራ ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት በጉልበት፣ገንዝብ፣ በስንቅና በማንኛውም ጉዳይ ድጋፍ እናደርጋለን ከጎኑም እንቆማለን" ሲሉም ገልጸዋል።

አጋጣሚውን ተጠቅመው በንግድ እቃዎች ላይ ዋጋ የሚጨምሩና የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ አንዳንድ ነጋዴዎች እነሱን እንደማይወክሉና በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ  ተናግረዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አበበ ተፈራ በበኩላቸው "ሰላማችን ከእጃችን እንዳይወጣ የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ሰላማችንን እንጠብቃለን" ብለዋል።

ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ሰላማቸውን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት በጋራ ለማስከበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ የከተማችንን ሰላም ለማጠናከር ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን ያሉት ደግሞ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሶፍያ ዓሊ ናቸው።

ጥያቄ ያለው አካል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቹን በውይይትና በንግግር መፍታት እንዳለበት  አሳስበው፣ መንግስትም የህዝብን ጥያቄዎች በየደረጃው ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የምስራቅ አማራ ሪጅን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ እድገትና የሕዝብ አንድነት ምቾት ያልሰጣቸው እነዚህ ጠላቶች ሕዝቡን በብሔር፣ በእምነትና በሌሎችም በመከፋፈል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው ብለዋል።

"በመሆኑም ሁሉም በየአካባቢው ሰላሙንና አንድነቱን በመጠበቅ ለአገር ሰላም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል" ሲሉ አሳስበዋል።

"ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም" ያሉት ሌተናል ጀነራሉ ይህን ለማስቀረት ሰላምን መጠበቅ፣ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንግድና በውይይት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁሌም ችግሮችን በውይይት መፍታት አገርና ሕዝብን እንደሚጠቅም በማስገንዘብ። 

ሕብረተሰቡ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን ፍቅርና ክብር በተግባር እየገለጸና እያሳየ በመሆኑ አመስግነው፣ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም