ቀጥታ፡

የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ አለባቸው-የአፍሪካ ኅብረት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 10/2015(ኢዜአ):-አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የአፍሪካ አገራት ለዘርፋ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ማስፋት እንደሚገባቸው የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ገለጹ።

አምባሳደር ጆሴፋ በነሐሴ ወር መጨረሻ በኬንያ ናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚካሄደውን አህጉራዊ ጉባኤ አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ነው ብለዋል።

በዚህም የተነሳ አፍሪካዊያን ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ጠቅሰው ይህንንም ለመቀልበስ የአፍሪካ ሕብረትና አባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የአፍሪካ አገራት አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዘርፋ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ በጀታቸው በአማካይ 2 በመቶ መሆኑን ገልጸው ችግሩን በአግባቡ ለመከላከል በጀቱ ቢያንስ 10 በመቶ መድረስ እንዳለበትም ተናግረዋል።

አፍሪካ የካርበን ልቀቷን ሳትጨምር ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አሟጣ በመጠቀም አህጉሪቱ አሁን ላይ ድህነትን ጨምሮ የሚገጥሟትን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፈተናዎች ማለፍ ትችላለች ነው ያሉት ኮሚሽነሯ።

ይህም አህጉሪቱ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገው ድጋፍ ላይ ያላትን ተስፋ በራሷ አቅም ችግሯን ለመፍታት ያስችላታል ብለዋል።

35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ዙሪያ እንዲደረግ የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ኬንያ ጉባኤውን ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1/2015 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ታካሂዳለች።

ጉባኤው የአፍሪካ ሕብረትና የሕብረቱ አባል አገራት እንዲሁም አጋር አካላት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ዳግም ቃል ኪዳናቸውን የሚያድሱበት ነው ተብሏል።

እንዲሁም በዘርፋ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር እንደሚያስችል የተገለጸ ሲሆን ጉባኤው እስከ አሁን የተከናወኑ ስራዎችን ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም