ቀጥታ፡

በዞኖቹ በመኸር አዝመራ 850 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለምቷል

ጊምቢ/ ሻሸመኔ ፤ ነሀሴ 10/2015(ኢዜአ)፡- በምዕራብ አርሲና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በመኸር አዝመራ 850 ሺህ ሄክታር መሬት ገደማ በተለያዩ የሰብል አይነቶች መልማቱን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን የግብርና ፅሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሳ፣ በ2015/16 ምርት ዘመን 312 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራም ከ377 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ማልማት እንደተቻለ ገልጸዋል።

እየለሙ ካሉት ሰብሎች መካከል በዞኑ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ ሩዝን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች ይገኙበታል ብለዋል።

በምርት ዘመኑ እየለሙ ካሉ ሰብሎች ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰበሰብ መታቀዱንም አስረድተዋል።

ከአዝመራው የተሻለ ምርት ለማግኘትም 180 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማደበሪያ በማዘጋጀት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

በዚሁ መሰረት በዘንድሮ በልግና የመኸር አዝመራ ከ9 ሚሊየን ሜትር ኪዪብ በላይ የተለያየ የተፈጥሮ ማደበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮችም የተለያዩ የግብርና ዘዴዎችን ተጠቅመው ምርትና ምርታመነትን ለመጨመር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የጊምቢ ወረዳ የጆግር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሆርዶፋ ተፈራ፣ የእርሻ ስራን በተለመደ አሰራር ሲያከናውኑ በመቆየታቸው ተጠቃሚ እንደልነበሩ ተናግረዋል።

በዘንድሮ መኸር አዝመራ መሬታቸውን በሩዝና ቦቆሎ ማልማታቸውን ገልጸው፤ የተሻለ ምርት ለማግኘት በግብርና ባለሙያ ምክር በመታገዝ ሰብሉን እየተንከባከቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የላሎ አሳቢ ወረዳ አሌ ቀበሌ ነዋሪ ታከለ ሞቲ በዘንድሮ መኸር አዝመራ ከአካባቢያቸው አስር አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ቦቆሎ እያለሙ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ አርሲ ዞን በዘንድሮ የመኸር አዝመራ እስካሁን ድረስ 470 ሺህ ሔክታር መሬት  ታርሶ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብዱለጢፍ ከድር እንዳሉት በዞኑ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 484 ሺህ 747  ሄክታር መሬት ነው።

እስካሁን 470 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በማሽላ፣ በቦቆሎ፣ በጤፍ፣ በገብስና በሌሎችም የሰብል ዓይነቶች እየለማ ነው ብለዋል።

ምርቱ ገበያና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ ከወዲሁ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር የሚያስተሳስር አደረጃጀት መፈጠሩንም አመልክተዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች በዘር ለሸፈኑት መሬት 440 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 90 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ተጠቅመዋል ነው ያሉት። 

በልማቱ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል የሲራሮ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት በ4 ሔክታር መሬታቸው ላይ  ለቀለብና ለገበያ የሚሆኑ ሰብሎችን በመዝራት ላይ ናቸው።

በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ  ማሾ እና ማሽላ መዝራታቸውን ገልጸው ጤፍም ለማልማት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮፈሌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ አደም በ6 ሄክታር ማሳ ላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው ስንዴ እና ቦቆሎ መዝራታቸውን አመልክተዋል።

በተለይ የስንዴ ምርት በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ እና ከሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

በዞኑ በተያዘው መኽር ምርት ከሚለማው መሬት 15 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም