ኢትዮጵያ ከፊሊፒንስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አላት - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከፊሊፒንስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አላት - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 10/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከፊሊፒንስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሻ በፊሊፒንስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሰየሙት ደሴ ዳልኬ ገለጹ።
አምባሳደር ደሴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ሮሙዋልዴዝ ማርኮስ ጁኒየር አስገብተዋል።
ኢትዮጵያ እና ፊሊፒንስ ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማስፋት የሚችሉባቸው አማራጮች እንዳሉ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
መንግስት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ፊሊፒንስ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ካላት ልምድ አኳያ የአገሪቷ የንግድ ሰዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በአየር ትራንስፖርት መስክ ያላቸውን ትስስርም ማጎልበት ይገባቸዋል ነው ያሉት አምባሳደር ደሴ።
ኢትዮጵያ ፊሊፒንስ ጋር ካላት የልማት እድገት፣የንግድ እና ኢንዱስትሪ መስኮች ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግምና ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትም ለማጠናከር እንደምትሰራ ተናግረዋል።
የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ሮሙዋልዴዝ ማርኮስ ጁኒየር ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በንግድ፣ ቴክኖሎጂና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማስፋት የሚችሉባቸው አማራጮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
አገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስራቸውን በማጠናከር ግንኙነታቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን ኢዜአ ከፊሊፒንስ ዜና አገልግሎት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ መቀመጫቸውን በኮሪያ ሪፐብሊክ አድርገው ኢትዮጵያ ከፊሊፒንስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይሸፍናሉ።