ለአወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት ህንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ) ፦ አወሊያ የእርዳታና የልማት ድርጅት ለሚገነባው ባለ 19 ወለል ህንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

የመሠረት ድንጋዩን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የዓለም አቀፉ ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ዶክተር መሀመድ ቢን አብዱልከሪም ኢሳ እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የክብር ዶክተር ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ አስቀምጠዋል።

በ1 ሺህ 445 ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባው ይህ ህንጻ በ19 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገነባም ነው የተገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ “ለዘመናት ትውልድን በመደገፍ ለሚታወቀው አወሊያ የሚደረገው ይህ ድጋፍ የትብብር እና የአንድነት ማሳያ ነው” ብለዋል።

የሕንፃ ግንባታው የትውልድ ቀረጻ ስራውን በመደገፍ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጓዳኝ ትምህርት ቤቱን በገቢ ለመደገፍ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል፡፡

የህንጻ ግንባታው ሲጠናቀቅም የአካባቢውን ገጽታ በመቀየር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሚያላብሳት ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የክብር ዶክተር ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የዓለም አቀፉ ሙስሊም ሊግ ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

ለአወሊያ ዕርዳታና ልማት ድርጅት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የዓለም አቀፉ ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ዶክተር መሀመድ ቢን አብዱልከሪም ኢሳ ኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻልና አብሮነት ተምሳሌት መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም