ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እንሰራለን  - በደብረብርሃን የመንግስት ሰራተኞች

 ደብረብርሀን፤ ነሐሴ  9/  2015(ኢዜአ) ፡- በአካባቢያቸው የሰፈነው ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልና  በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊስተዋሉ የሚችሉ  ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ  የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አስታወቁ። 

“መከላከያችን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋስትና ነው ”በሚል መሪ ሀሳብ የመንግስት ሰራተኞቹ  በሰላም ዙሪያ  ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት፤ በሰላም ጊዜ  የሰላምን ዋጋ ማወቅ እንደማይቻል የተረዳሁት በሳለፍነው ሳምንት በነበረው  የሰላም እጦት ነው ሲሉ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የደብረብርሀን ከተማ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ  የመንግስት አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር   በሰላም ዙሪያ መወያያት መጀመራቸው  የመከላከያ ሰራዊቱ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠልና  በመንግስት  አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊስተዋሉ የሚችሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቀዋል።

የአካባቢያችንን ሰላም በማስጠበቅ  ህብረተሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል የድርሻዬን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ ያሉት ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ሸዋ ፈራ  ገዛኸኝ ናቸው ።

ግጭቱ በመንግስት ሰራተኞችና በተለያዩ የሙያ መስክ የተሰማሩ የማህበረሰብ ክፍሎች  ሰርተው  እራሳቸውን  እንዳይመሩ  ችግር ፈጥሮ እንደነበር አውስተዋል።

ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የአካባቢውን ሰላም አጽንቶ ለማቆየት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ  በትኩረት  እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባልና የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፤  የደብረብርሀን ከተማ  የፀጥታ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን  መሻሻሉን አስታውቀዋል። 

ከመንግስት ሰራተኞች ጋር የተደረገው ውይይት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሙሉ አቅም እንዲፈታ ለማስቻል የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች በሰላም ላይ ግንባር ቀደም ተምሳሌት በመሆን  ህብረተሰቡን በማንቃትና  በማስገንዘብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል።

በውይይቱ የተገኙ ገንቢ ሀሳቦችን በመጠቀም  ለሀብረተሰቡ ቀልጣፋና  ግልጽ  አገልግሎት በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና  ልማት ሁሉም እንዲረባረብም አሳስበዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም