ቀጥታ፡

የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን አረጋገጡ

ደሴ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ) ፦ የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእርድ ሰንጋዎችንና የፍየል ሙክቶችን ዛሬ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት የወሎ ህዝብ ጥንት ጀምሮ የሀገር ደጀን የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚያከብርና የሚደግፍ ህዝብ መሆኑን ገልጿል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሰይድ የሱፍ ድጋፉን ለሠራዊቱ ሲያስረክቡ እንደገለጹት የወሎ ህዝብ ባህልና እሴቱን ጠብቆ ለሀገር መከታና ኩራት ለሆነው መከላከያ ሰራዊቱ አጋርነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡

ህዝቡ በህግ ማስከበር ዘመቻም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በየግንባሩ መዋደቁን አስታውሰው፤ አሁንም ለጭንቅ ቀን ደራሽ ለሆነው ሠራዊት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡


 

ምክትል ከንቲባው አክለውም የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ ህዝብ ዛሬም 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 23 ሰንጋዎችን፣ ስድስት የፍየል ሙክቶችን፣ 12 ኩንታል በሶና ሌሎች ድጋፎችንም አድርጓል፡፡

ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን እየጠበቀ የአካባቢውን ሰላም ከሠራዊቱ ጋር በማስጠበቅ ፊቱን ወደ ልማቱ እያዞረ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለጹት የወሎ ህዝብ ጥንት ጀምሮ የሀገር ደጀን የሆነውን መከላከያውን የሚያከብርና የሚደግፍ ህዝብ ነው።


 

በህልውና ዘመቻው ወቅትም ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ በየተራራው የተዋደቀና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበረ ጀግና ህዝብ መሆኑን አስታውሰው፤ ለሠራዊቱ ሞራልና ወኔ እየፈጠረለት ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ለሠራዊቱ ስንቅ አዘጋጅቶ በማቅረብ ግዳጁን በአጭር ጊዜ እንዲወጣ እያደረገ ነው ያሉት ብርጋዴር ጄነራሉ ዛሬም ለሠራዊቱ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች በሐሰት ወሬ የሠራዊቱን ስም ለማጠልሸት ቀን ከሌት ቢሰሩም ህዝቡ ግን ከሠራዊቱ ጎን መሰለፉን በድጋፉ እያረጋገጠና ደጀን እየሆነ ነው ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም መጠበቅና አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥመው ለፀጥታ መዋቅሩ ጥቆማ በመስጠት ህግ እንዲከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም ብርጋዴር ጄኔራሉ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም