ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክትን የግንባታ ሒደትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 09/2015(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክትን የግንባታ ሒደት ጎበኙ።

ከንቲባዋ “ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ታሪክም እየገነባን ነው” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የአድዋ ድልን ታሪካዊ ዳራ መነሻ አድርጐ እየተገነባ የሚገኘው አድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም የኢትዮጵያ ጀግኖችንና የአድዋ መልክዓ ምድርን በሚገልፅ መልኩ ታሪካዊ እሴቱን ጠብቆ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ሙዚየሙ በከተማችን ውስጥ እስከ ዛሬ ከተገነቡ እና በመገንባት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ግዙፉ ሲሆን 11 ብሎኮችን የያዘና ሰፊ ቦታ ላይ እየተገነባ ያለ በውስጡም የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የአድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ እና የአንድነት ማዕከል እንደሚያካትትም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጀግኖችን ጉዞ የሚያሳይ ሙዚየም ፣ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ300 እስከ 4000 ሰው ድረስ የሚይዙ የተለያዩ አዳራሾች የሚገኙበት ሲሆን ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት የሚደረግ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

መጪውን የአድዋ በዓልም የጥቁር ህዝቦች የድል የታሪክ ከፍታን በሚመጥን መልኩ በዚሁ ስፍራ ላይ በጋራ እናከብራለን ሲሉም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም