አዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ገለጻ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ገለጻ ተደረገ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ)፡-አዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ገለጻ ተደርጓል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ጥሩ ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ በክልሉ ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ሰራዊቱና የክልሉ ሕዝብ ተቀናጅተው በመስራታቸው ችግር በነበረባቸው የክልሉ ከተሞች አንጻራዊ ሰላም ማግኘታቸውን አመልክተዋል።
“በክልሉ ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተከበረውን የአማራን ሕዝብ የማይወክሉ ናቸው” ያሉት ሜጄር ጄነራል ተሾመ ሰራዊቱ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወታደራዊ አታሼዎች የአገር የፀጥታ ጉዳይ በተመለከተ በየማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ለማጥራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ከመከላከያ ወታደራዊ አመራሮች እውነተኛ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉም ነው ሜጄር ጄነራሉ የገለጹት።
የመከላከያ የውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ከወታደራዊ አታሼዎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም ገልጸዋል።
የየአገራቱ ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላይ ያለው የፀጥታ ችግር መንስኤና አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ በተደረገው ገለጻ ትክክለኛ መረጃ አግኝተናል ብለዋል።
መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱ እንዲሁም ሕዝቡ ለሰላም መከበር ያሳዩትን ቁርጠኝነት አታሼዎች እንዳደነቁም ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።