ኢትዮጵያና ሕንድ ያላቸው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጠናክር መልኩ ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል- አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሕንድ ያላቸው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጠናክር መልኩ ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል- አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሕንድ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት የአገራቱን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት በሚያጠናክር መልኩ ይበልጥ መጎልበት እንደሚገባው በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገለጹ።
“ኢትዮጵያ የሕንድ ሕዝብ በጥንካሬ እና በጽናቱ ላረጋገጠው ነጻነት ትልቅ ክብር አላት” ብለዋል።
ሕንድ 77ኛውን የነጻነት በዓል ዛሬ በማክበር ላይ ትገኛለች።
በዓሉን በማስመልከት በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ ወቅት በሃገራቱ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ በወዳጅነት ላይ የተመሰረተውንና እየጎለበተ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት መለስ ብሎ መመልከት ተገቢ መሆኑን አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገልጸዋል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጋራ እሴቶች፣ በመከባበርና በጠንካራ የባለ ብዙ ወገን ትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይም የአገራቱ ትስስርና ትብብር ይበልጥ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል።
“የሕንድ ሕዝብ ነጻነቱን ለማግኘት ለከፈለው ዋጋ፣ ላሳየው ጽናትና ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ ትልቅ አክብሮት አላት” ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የነጻነት በዓሉ ለሕንዳውያን የሰላምና የደስታ እንዲሆን ምኞታቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ በኒው ዴልሂ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
All reactions:
5050

