ከ39 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የገበያ ፈቃድ ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ከ39 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የገበያ ፈቃድ ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015(ኢዜአ)፡-በ2015 በጀት ዓመት ከ39 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ፡፡
አዲስ አበባ ነሀሴ 9/2015 የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻፀም አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የባለስልጣኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበራ ደነቀ፤ በመግለጫቸው የምግብና መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የትምባሆና አልኮል እንዲሁም የኮስሞቲክስ ምርቶች ላይ የቁጥጥር ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ጥራት በማረጋገጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ከ39 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።
በተጨማሪም 867 መድኃኒቶችንና 1 ሺህ 259 የህክምና መሳሪያዎችን በመመዝገብ የገበያ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በባለስልጣኑ የገበያ ፈቃድ የተሰጣቸው መድኃኒቶችን ቁጥር 3 ሺህ 845 ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ546 የመድሀኒቶች፣ ለ49 የህክምና መሳሪያዎች እና ለ104 የመዋቢያ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች አዲስ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
የተበላሹና የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ ግብዓቶችና የህክምና መሳሪያዎች እና የተለያዩ ምግቦች በጉዞ ላይ እያሉ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የተለያዩ ምርቶች ላይ የናሙና ፍተሻ በማድረግ በህገ ወጥ ተግባር በተሰማሩ አካላት የተቀናጀ ክትትልና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።